Fana: At a Speed of Life!

ኤጀንሲው ዳያስፖራው የሚሳተፍባቸው የንግድና ኢንቨስትመንት ፓኬጆች እንደሚዘጋጁ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ የሚኖሩና አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዳያስፖራዎች የሚሳተፉባቸውን የንግድና ኢንቨስትመንት ፓኬጆች እንደሚያዘጋጅ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው የብድር አማራጭ ከሚያመቻቹ ባንኮችና የቢዝነስ ሀሳብ ካላቸው የመንግስት አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተቋማት ጋር ምክክር አድርጓል።

ምክክሩ በዋናነት አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውና በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ የሚገኙ ዳያስፖራዎች በአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሰማሩ ለማስቻል ያለመ ነው።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እንዳሉት በአገራዊ የልማት ስራዎች በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ የሚገኙ ዳያስፖራዎች ተሳትፎ ከፍተኛ ነው።

ገቢያቸው አነስተኛ ቢሆንም በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በከፍተኛ ሁኔታ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

ይህ የሚያሳየው ከብዛታቸው አንጻር ብዙ ሀብት መኖሩንና በአንድ ላይ በማሰባሰብ በፓኬጅ ቢደራጁ ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ውጤት እንደሚያመጡ ነው ብለዋል።

በአገር የኢኮኖሚ ዕድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ የኢንቨስትመንት አማራጮች ሊቀርብላቸውና እነሱን የሚመጥኑ የንግድና ኢንቨስትመንት ፓኬጆች ሊፈጠሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የፓኬጁ መዘጋጀት ዳያስፖራዎቹ ያካበቱትን ገንዘብና ልምድ ለአገራቸው እድገት እንዲያውሉትና ሀብታቸውም እንዳይባክን ይረዳል ነው ያሉት።

በመሆኑም ባለድርሻ አካላቱ ፓኬጆችን ለማዘጋጀት በሚያስችሉት ጉዳዮች ሃሳብ እንዲያመነጩና በጋራ እንዲሰሩ ዋና ዳይሬክተሯ ጥሪ ማቅረባቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የዳያስፖራውን የዕድገት ደረጃ የሚመጥኑ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማቅረብ እንደሚገባም የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ኦላኒ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በአገሪቱ የንግድ ፈቃድ ከመስጠት ውጭ አነስተኛና መካከለኛ ዘርፉን ማስተናገድ የሚያስችል አሠራር እንዳልነበረም ገልጸዋል፡፡

አሁን አገሪቷ በደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ልክ ፍላጎቱን ማስተናገድ የሚያስችሉ ፓኬጆች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

በኢተዮጵያ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ሊሳተፍ የሚችልባቸው የጨርቃ ጨርቅ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶችና የግብርናና ገጠር ልማት ዘርፎች መኖራቸውንም አቶ ዳንኤል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአገር ልማት ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.