Fana: At a Speed of Life!

እነ ሜጀር ጄኔራል ገብረመድህን ፍቃዴ (ወዲነጮ) ክስ ሊመሰረትባቸው ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ሬዲዮ ግንኙነትን በማቋረጥ በሰሜን ዕዝ ጦር ላይ ጥቃት እንዲደርስ አድርገዋል የተባሉት የመከላከያ ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ እነ ሜጀር ጄኔራል ገብረመድህን ፍቃዴ (ወዲነጮ) ክስ ሊመሰረትባቸው ነው፡፡

በዛሬው ዕለት በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ መመስረቻ ጊዜ ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡

ክስ መመስረቻ የተጠየቀባቸው ተጠርጣሪዎቸ የመከላከያ ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ገብረመድህን ፍቃዴ፣ ሜጀር ጄኔራል ይርዳው ገብረመድህን፣ ብርጋዴር ጄኔራል አብርሃም መውጫ፣ ኮሎኔል ገብረህይወት ደስታ፣ ኮሎኔል ዮሃንስ በቀለ፣ ኮሎኔል ዘመን ታመነ ፣ ሻለቃ ገብረእግዚአብሄር ግርማይ፣ ሌተናል ኮሎኔል ተክለ ኃይሉ፣ ሌተናል ኮሎኔል ምሩጽ ወልደአረጋይ፣ ሻለቃ ኃይለስላሴ ግርማይ እና ሻለቃ ብርኃኔ ገብሩ ናቸው፡፡

እነዚህ ተጠርጣሪዎች በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቡድን በተጠረጠሩበት ህገመንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ ሙከራ ወንጀል ምርመራ ሲደረግባቸው መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

ይሁንና ምርመራው መጠናቀቁን ተከትሎ ዐቃቤ ህግ ክስ መመስረቻ ጊዜ ጠይቆባቸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም ተጠርጣሪዎቹ ከዚህ በፊት የተጠየቀባቸውን የጊዜ ቀጠሮ ከየካቲት 20 ቀን ጀምሮ ለምርመራ ተብሎ የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶ ስለነበረ ይህን ታሳቢ ተደርጎ ዐቃቤ ህግ ከጠየቀው 15 ቀናት ውስጥ 10 ቀናት ፍርድ ቤቱ በመፍቀድ ክስ እንዲመሰርት የምርመራ መዝገቡን መዝጋቱን አስታውቋል፡፡

ይሁንና ዐቃቤ ህግ በተጠቀሰው ጊዜ ከስ ካልመሰረተ በሌላ መዝገብ ተጠርጣሪዎቹ መብታቸውን መጠየቅ ይችላሉ ተብሏል፡፡

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.