Fana: At a Speed of Life!

እነ ስብሃት ነጋ ጉዳያችን በትግራይ ክልል ፍርድ ቤት ይታይልን በሚል ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ ሆነ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2013 (ኤፍቢሲ) እነ ስብሃት ነጋ በትግራይ ክልል ፍርድ ቤት ጉዳያችን ይታይልን ሲሉ ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ ሆነ፡፡

ባለፈው ቀጠሮ ተጠርጣሪዎቹ ጉዳያችን በፌደራል ፍርድ ቤት ሳይሆን በትግራይ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው መታየት ያለበት ሲሉ አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡
አቤቱታውን የተመለከተው ፍርድ ቤትም ጉዳያቸው መታየት ያለበት አካባቢ ወሰን ሳይደረግበት ወንጀሉ ሲፈፀምም ከክልሉ ውጪ ማለትም ባህር ዳርና ጎንደር በሮኬት የተመታ እና በሃገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት የደረሰ በመሆኑ እንዲሁም የፌደራል መንግስትን ስልጣን በሃይል ለመቆጣጠር የተፈፀመ ወንጀል በመሆኑ የአካባቢ የዳኝነት ስልጣን ያለው የፌደራል ፍርድቤቶች ነው ሲል ጥያቄቸውን ውድቅ አድርጎታል፡፡
በዛሬው ችሎት አቶ ስብሃት ነጋ፣ አምባሳደር አዲስአለም ባሌማ፣ አምባሳደር አባይ ወልዱ፣ዶክተር
አብርሃም ተከስተን ጨምሮ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡
ነገር ግን ዶክተር ግዳይ በርሄና አባዲ ዘሙን ጨምሮ ሌሎች ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች በህመም ምክንያት ችሎት አለመቅረባቸው ተገልጿል፡፡
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ተጠርጣሪዎች ያነሱትን አቤቱታ ተከትሎ ብይን ሰጥቷል፡፡
በዚህ መሰረትም ዐቃቤ ህግ የቅድመ ምርምራ ምስክር እንዲሰማ የመወሰን ስልጣን የለውም ብለው ባነሱት መቃወሚያ ላይ ፍርድ ቤቱ ቀዳሚ ምርመራ የመወሰን ስልጣን የጠቅላይ አቃ ህግ ነው ሲል መቃወሚያውን ህጋዊ መሰረት ያለው ሆኖ አላገኘሁትም በማለት ውድቅ አድርጎታል፡፡
እንዲሁም በወንጀል ስነ ስርዓት ህጉ አንቀፅ 80 ንዑስ ቁጥር 1 መሰረት በከባድ ወንጀልና የግፍ ግድያ ቀዳሚ ምርመራ የሚደረግ መሆኑን የመወሰን ስልጣን ለዐቃቤ ህግ እንዲሰጠው ችሎቱ አብራርቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የምስክር ስም ዝርዝር ይገለፅልን ብለው ባቀረቡት አቤቱታ ላይም በምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699 መሰረት ምስክሮች ለደህንነታቸው ሲባል ማንነታቸው ሳይታይ ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ የተደረገ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም በማለት ውድቅ አድርጎታል፡፡
በዚህ መሰረትም ለዝግ ችሎት የዐቃቤ ህግ የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት ለመጋቢት 29 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በቀጣይ ቀጠሮም ማረሚያ ቤቱ ዛሬ ችሎት ያልተገኙ ተጠርጣሪዎችን እንዲያቀርብ አዟል፡፡
በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.