Fana: At a Speed of Life!

እነ አቶ ስብሃት ነጋ ጉዳያችን በትግራይ ክልል ፍርድ ቤት ይታይልን ሲሉ አቤቱታ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2013 (ኤፍቢሲ) እነ አቶ ስብሃት ነጋ ጉዳያችን በትግራይ ክልል ፍርድ ቤት ይታይልን ሲሉ አቤቱታ አቀረቡ፡፡

ይህን አቤቱታ ያቀረቡት ዛሬ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድቤት አራዳ ምድብ ችሎት ነው።

በችሎት የተገኙት የጠቅላይ አቃቤ ህግ ቡድን በበኩሉላቸው የፌዴራል መንግስትን ስልጣን ለመጣል በሚል የሽብር አዋጁን በመተላለፍ በመላው ሀገሪቱ የተፈጸመ ወንጀል መሆኑን በመጥቀስ ተጠርጣሪዎቹ መቀሌ ሆነው በሰጡት ትዕዛዝ ባህርዳር እና ጎንደርን በሮኬት ማስደብደባቸው አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ተከሳሾቹ ስልጣን ተከፋፍለው በተለያዩ ቦታዎች የተፈጸመ ወንጀል ነው ያለው  አቃቤ ህግ  ዶክተር አዲስ አለም ባሌማ የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ሆነው አዲስ አባባ ቁጭ ብለው ሲፈጽሙ የነበረው ወንጀል አንድ ቦታ አለመሆኑን ማመላከቻ ነው ብሏል በምላሹ።

ይህ የሚያሳየው በሃገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች መፈጸማቸውን ስለሆነ በአካባቢ ስልጣን ሳይገደብ ጉዳያቸው መታየት ያለበት በፌዴራል ፍርድ ቤት ነው ሲል በጠበቆቻቸው ያነሱት መከራከሪያ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች ቀዳሚ ምርመራ መደረግ የለበትም አቃቤ ህግም ቀዳሚ ምርመራ  እንዲደረግ ያዘዘው ትዕዛዝ አግባብነት የለውም የቀዳሚ ምርመራ ህጉ ተሽሯል ብለው ያነሱት መቃወሚያ በተመለከተም፤ አቃቤ ህግ  በቂ ምክንያት ካለው በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህግ  አንቀጽ 38 ቀዳሚ ምርመራ ማድረግ ይችላል ብሏል።

እንዲሁም በአንቀጽ 80 ንኡስ አንጽ 2 ስር ህጉን ተከትሎ የቀዳሚ ምርመራ የመወሰን ስልጣን እንዳለው ያስቀምጣል ሲል አብራርቷል።

የቀዳሚ ምርመራ ህግ ሙሉ ለሙሉ አልተሻረም በስራ ላይ ይገኛል ሲል ምላሽ የሰጠው አቃቤ ህግ፤ የውንብድና ወንጀል እና የግፍ ግድያ የተፈጸመ ከሆነ ቀዳሚ ምርመራ ሊደረግ እንደሚችል በህጉ ያስቀምጣል ሲል የአቃቤ ህግ ቡድን ምላሽ ሰጥቷል።

በተጨማሪም የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮች ስምና ዝርዝሩ አልተገለጸም እዚህ ላይ ትዕዛዝ ይሰጥልን ሲሉም ላቀረቡት አቤቱታ አቃቤ ህግ የምስክር ጥበቃ አዋጅን  ተከትሎ ለምስክሮ ደህንነት ሲባል የስም ዝርዝራቸው እንደማይሰጥ አብራርቷል።

ከዚሀም ባለፈ የተጠርጣሪ ጠበቆች ዳኛው ከዚህ በፊት በነበረ የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይን ሲመለከቱ መዝገባችን ተለይቶ ይቅረብ ብለን የጠየቅነው ጥያቄ ሳይታይ አልፏል የሚል ምክንያት በማንሳት ዳኛው ከዚህ ከቀዳሚ ምርመራ መዝገብ ይነሱልን ሲሉም አመልክተዋል።

እንዳጠቃላይ በተነሱ መከራከሪያ ነጥቦች ላይ ፍርድቤቱ ምርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለመጋቢት 17 ቀን 2013 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን፤  በትናንትናው እለት ችሎት ከደንበኞቻቸን ጋር ባልተመካከርንበት ሁኔታ ምስክር መሰማቱ ተገቢ አይደለም ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን ብለው ያቀረቡት አቤቱታን መርምሮ ችሎቱ የመመካከሪያ በቂ የ7 ቀን ጊዜ  ሰጥቻለሁ ሲል ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጓል።

ችሎቱ አቶ ስብሃት በግል ሃኪም እንዲታከሙ የታዘዘው ትዕዛዝ ተፈጻሚ እንዲሆን አዟል።

አምባሳደር አባይ ወልዱ ለዐይናቸው ህመም በግል እንዲታከሙ ያቀረቡት አቤቱታን ተቀብሎ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

 

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.