Fana: At a Speed of Life!

እንቦጨን ከጣና ሃይቅ ለማስወገድ የሚካሄደውን ዘመቻ ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) እንቦጨን ከጣና ሃይቅ ለማስወገድ የሚካሄደውን ዘመቻ በይፋ ለማስጀመር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ዘመቻው የፌደራሉና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ  ኃላፊዎች በተገኙበት የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 9 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር እንደሚካሄድ መገለፁ ይታወሳል።

በዘመቻው ትግበራ ላይ የሚከናወኑ ዝርዝር  ተግባራትን አስመልክቶ  የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከተፋሰስ ልማት ባለስልጣን አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር ተወያይተዋል።

አረሙን ከውሃው ላይ ለማስወገድ አስፈላጊ የሆኑ ገልባጭ ተሸከርካሪዎች፣ ማጨጃ መሳሪያዎች ሞተር ሳይክሎችና ጀልባዎች እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች የሚቀርቡበት መንገድም መመቻቸቱ በውይይቱ ተነስቷል።

ለዚህ ዘመቻ 95 ሚሊየን ብር የሚያስፈልግ ሲሆን፥  ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የገንዘብ  ድጋፉን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል።

በአሁኑ ሰአትም ለዘመቻው የሚያስፈልገውን ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ መጀመሩም ነው የተገለፀው።

በአሁኑ ሰአት የእንቦጭ አረም ሃይቁን በሚያዋስኑ 9 ወረዳዎች በሚገኙ 30 ቀበሌዎች  ላይም ተንሰራፍቶ ይገኛል።

እንቦጭ የተንሰራፋበትን የጣና የውሃ አካል ሁሉም ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ የፌደራል እና የክልል ተቋማት እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በመከፋፈል በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ የሚስወግዱት ይሆናል፡፡

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና  የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት  ክልሎችን በማስተባበር ለአንድ ወር የሚካሄደውን ዘመቻ የሚመሩትይሆናል።

ሁሉም ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ሁሉም ኢትዮጵያውያን በዘመቻው ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ መቅረቡንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.