Fana: At a Speed of Life!

እዉነተኛ ህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርዓትና ጠንካራ ሃገራዊ አንድነት የማይዋጥላቸዉ የግለሰቦች ስብስብ የለዉጥ ጮራዉን ለማጨለም ሌት ተቀን እየሰራ ይገኛል – የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)እዉነተኛ ህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርዓትና ጠንካራ ሃገራዊ አንድነት የማይዋጥላቸዉ የግለሰቦች ስብስብ የለዉጥ ጮራዉን ለማጨለም ሌት ተቀን እየሰራ እንደሚገኝ የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ አስታወቀ።
 
በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ መግለጫ ሰጥቷል።
 
ይህ ትልቅ ተስፋ የፈነጠቀዉና ሰፊ የህዝብ ድጋፍ ያልተለየዉ ታሪካዊዉ ለዉጥ፤የህዝቦች እኩልነት፤ የዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፤ እዉነተኛ ህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርዓትና ጠንካራ ሃገራዊ አንድነት የማይዋጥላቸዉ የግለሰቦች ስብስብ የለዉጥ ጮራዉን ለማጨለም ሌት ተቀን እየሰራ ይገኛል ብሏል ፓርቲዉ።
 
ይህ ከንቱ መፍጨርጨራቸዉ ከዉጭ ሃይሎች ሳይቀር በመመሳጠር ሃገር የማተራመስና ህዝብ ለህዝብ የማጋጨት እኩይ ዓላማ ያነገበ መሆኑ የጉዳዩን ክብደትና አሳሳቢነት ከፍ ያደርገዋል ይላል መግለጫው፤
 
ከነዚህ በተሻለ ሃሳብና የፖለቲካ ዉድድር የተሸነፉና ሃገር የማመስና ህዝብ የማጋጨት ሴራ የተሸሸጉ ሃይሎች አንዱ የሆነዉ የህዉሃት ቡድን ነዉ ያለዉ መግለጫዉ በተራ ሽንፈት፤ በቀቢፀ-ተስፋዊ ጠብ አጫሪነትና ታሪክ ይቅር በማይለዉ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተግባር ላይ ተሰማርቶ ፤በትግሯይ ህዝብ ላይ መጠነ ሰፊ የቀቢፀ-ተስፋ ግፍ እየፈጸመ ይገኛል ሲል መግለጫው ይጠቁማል ።
 
ህዉሃት በዚህ ተግባሩም በክልል አማራጭ ሃሳብ እንዳይፈጠር የማድረግ እጅግ ኋላቀር በሆነ አስተሳሰብና ተግባር የለዉጥ ሃይሎች ናቸዉ ያላቸዉ ዜጎችና ቤተሰቦቻቸዉን የተለያዩ ስሞች በመለጠፍና በየስብሰባዉ እንዲሸማቀቁ የማድረግ ተግባር ላይ ይገኛል ብሏል ፓርቲዉ በመግለጫዉ።
 
የዜጎች በሰላምና በነጻነት የመኖር መብታቸዉን በመቀማት ከተከራዩበት የግለሰብ ቤት ሳይቀር በተከታታይ እንዲባረሩ የማድረግ፤ በግፍ የማሰር፤ድብደባና ከኑሯቸዉና ከንግድ ስራቸዉ እንዲፈናቀሉ በማድረግ ፤ ከዚህ በባሰም ከትዉልድ አካባቢዯቸዉ በሃይል ለቀዉ እንዲወጡ በማድረግ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ህዉሃት በትግራይ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ስለመሆኑም ፓርቲው በመግለጫው አሰታውቋል።
 
ለትግራይና መላ ኢትዮጵይዉያን ያለዉን የንቀት መጠን በሚያሳይ መልኩ በህገ-ወጥና በይስሙላ ምርጫ ስልጣኑን በማራዘም የትግራይን ህዝብ ለባሰ ጭቆኗና ብዝበዛ፤ ኢትየጵያ ሃገራችንን ደግሞ ለግጭትና እልቂት አጭቷታል ያለዉ መግለጫ ይህም የአፈና አገዛዙ ለማስቀጠል እንጂ ለትግራይ ህዝብም የሚጠቅም አጀንዳ ኖሮት አይደለም ይህንንም የትግራይ ህዝብም መላዉ ኢትዮጵይዉያንም የሚረዱት ሃቅ ነዉ ብሏል።
 
ስለዚህም የህዉሃትን የግፍ ስራዎች ለመግታት መንግስት የጀመረዉ ህግ የማስከበርና ፍትህ የማንገስ ወሳኝ ሃገራዊ ስራ አጠናክሮ እንዲገፋበትና የትግራይ ህዝብ እየደረሰበት ካለዉ አፈናና፤ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ዉንብድና የመከላከል ሃላፊነቱን አበክሮ እንዲከዉን ፓርቲዉ ጥሪዉን አቅርቧል።
የትግራይ ህዝብ በተለይ ወጣቱ በጊዜያዊ ጫናና ማስፈራሪያ ሳይደናገጥ፤ ለደረስንበት ጊዜና የለዉጥ ምዕራፍ ፍጹም የማይመጥነዉን የህዉሃት ኋላቀር ስርዓት በቃኝ በማለት ድምጹን እንዲያሰማና ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸዉን እንዲያስከብሩ ሲል ፓርቲዉ አሳስቧል።
 
የትግራይ ህዝብ በታሪኩ ለኢትዮጵየ ባበረከተዉ ጉልህ አስተዋጽኦና ለህዝብ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በከፈለዉ ከባድ መስዋዕትነት ልክ እንዲከበርና ተጠቃሚ እንዲሆን አዲሱ ትዉልድ የተሻለ መፃኢ እድልና ዘላቂ ሃገራዊ ተጠቃሚነትን እንዲቀዳጅ ትግሉን እንዲያቀጣጥል ፓርቲዉ ጠይቋል።
 
ይህ ህዝባዊ ለዉጥ እዉን እንዲሆንም የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከህዝባችን ጎን ቆመን የሚጠበቅብንን ቀዳሚ ግዳጅ ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆናችን ስንገልጽ በታላቅ ህዝባ ኩራትና የትግል ጽናት ታጅበን መሆኑን እንገልፃለን ብሏል የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ በመግለጫዉ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.