Fana: At a Speed of Life!

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሀገርን ሰላም ለማረጋገጥ በላቀ ደረጃ የድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል- አቶ ርስቱ ይርዳ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሀገርን ሰላም ዴሞክራሲና እውነተኛ ፌዴራሊዝም ለማረጋገጥ ድርሻው የላቀ መሆኑን በመረዳት ለዚህ መሥራት እንደሚገባው የደቡብ ክልል ርዕሠ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ ተናገሩ፡፡
ትኩረቱን በሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ፌዴራሊዝም ላይ አድርጎ በአርባምንጭ ከተማ የተካሄደው አምስተኛው ስለኢትዮጵያ የፓናል ውይይት ተጠናቋል፡፡
የፓናል ውይይቱን የመሩት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ÷ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሀገርን ሰላም ዴሞክራሲና እውነተኛ ፌዴራሊዝም ለማረጋገጥ ድርሻው የላቀ መሆኑን በመረዳት ለዚህ መሥራት ይገባዋል ብለዋል፡፡
ሰላምን መፈለግ ተገቢ እንደሆነ ጠቅሰው÷ ሰላም የሚጀምረው ከቤተሰብ መሆኑን በመረዳት፤ ለሠላም ሲባል ለራስም ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ዋጋ መክፈልን ይጠይቃል ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ሰላምን ማረጋገጥ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የቤትሥራ ነው ያሉት አቶ ርስቱ÷ አንጻራዊ በሆነ መልኩ በደቡብ ክልል ያለው ሰላም የመጣው ለባህላዊ እሴቶች ትኩረት መስጠት በመቻሉ፣ ከእናቶችና ከአባቶች ጋር በመቀራረብ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ለሀገር በቀል መፍትሄዎች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ጠቁመው÷ ያም ሆኖ ገና ቀሪ ስራዎች አሉብን ብለዋል።
የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ ይመልሳል ተብሎ የተጠበቀው ለውጥ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው÷ ዴሞክራሲው ወደኋላ እንዳይመለስ ሁሉም ኃላፊነት አለበት፤ ዴሞክራሲው ጽንፈኝነት እየተጫነው፤ በዴሞክራሲ ስም መብቴ ነው በሚል ሰበብ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳና እንዲጋጭ እየተደረገ ያለውን ሴራ በጋራ መመከት ይገባልም ነው ያሉት።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ÷ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም አብሮነትን የሚያበረታታና የሚያጠናክር በመሆኑ ከዚህ ውጭ ያሉት ድርጊቶች መጤ እንጂ የኢትዮጵያውያን አይደሉም ብለዋል።
አብሮ መኖር አብሮ ችግሮችን መጋፈጥ እንጂ መለያየት የፌዴራሊዝም መለያ ባህሪ አይደለም ሊሆንም አይገባምም ነው ያሉት፡፡
መንግስት ለሰላም ብዙ ርቀት ይጓዛል ያሉት ዶክተር ቢቂላ÷ከሚያለያዩን ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ጉዳዮች ብዙ ናቸውና እነሱ ላይ አጠንክረን መስራት ይገባናል ብለዋል በንግግራቸው።
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው÷ ሰላምን መፍጠር የመንግሥት ሥራ ብቻ አድርጎ መውሰድ ስህተት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ማንም ሰው ጥያቄ ሊኖረው ይችላል፤ ጥያቄው ዛሬ አሁኑኑ ይመለስ ማለት ግን ሀገርን የሚያፈርስ እንጂ ከዚህ የዘለለ ሚና ስለማይኖረው መታገስ አስፈላጊ ነው ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
በሌላ ጫፍ ላይ ያሉትን ኃይሎችም በሰላም ወደ መሃል ማምጣት ይገባል ያሉት ፕሮፌሰር በየነ÷ ለዚህ ሰላም ሲባል ተሸናፊ ሆኖ ታግሶ ዋጋ መክፈል ይገባል ነው ያሉት፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.