Fana: At a Speed of Life!

እያጋጠመ ያለውን የኃይል መቆራርጥ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት እና በዲስትሪቢዩሽን መስመሮች እርጅና ምክንያት የሚከሰተውን የኃይል መቆራረጥና መዋዥቅ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የዲስትሪቢዩሽን መስመሮች ማሻሻያና ማስፋፊያ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የማሻሻያ ሥራው በሶስት ሎት ተከፍሎ በቻይና እና በህንድ ተቋራጮች አማካኝነት እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሎት 1 ወላይታ ሶዶና ሐረር ከተሞች ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የማሻሻያ ስራ 166 ነጥብ 72 ኪሎ ሜትር ባለ 15 ኪሎ ቮልት የመካከለኛ መስመር ማሻሻያ ግንባታና ነባር መስመሮችን መጠገን፣ 132 ኪሎ ሜትር ባለ 0 ነጥብ 4 ኪሎ ቮልት የዝቅተኛ መስመር ማሻሻያ ግንባታና ነባር መስመሮችን የማንሳት፣ 25 ነባር የዲስትሪቢዩሽን ትራንስፎርመሮች ማሻሻያ ሥራ፣ የ40 አዲስ የዲስትሪቢዩሽን ትራንስፎርመሮች ተከላ እና የ8 ሺህ 773 የኮንክሪት ምሰሶ ተከላ ስራ ለማከናወን ታቅዶ 5 ሺህ 47 (የኮንትራቱን 59 ከመቶ) የመካከለኛና የዝቅተኛ መስመር የኮንክሪት ምሰሶዎች የጥራት ፍተሻ አልፈው ወደ ሳይት መጓጓዛቸው ተገልጿል፡፡
ከዚህ ውስጥ የ4 ሺህ 535 (የኮንትራቱን 54 ከመቶ) የዝቅተኛና መካከለኛ መስመር ኮንክሪት ምሰሶ ተከላ መከናወኑም ተመላክቷል፡፡
በሎት 2 የሻሸመኔ እና በደብረማርቆስ ከተሞች ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የማሻሻያ ስራ የ194 ነጥብ 73 ኪሎ ሜትር ባለ 15 ኪሎ ቮልት የመካከለኛ መስመር ማሻሻያ፣ ግንባታ፣ ነባርና መስመሮችን የማንሳት፣ የ141 ነጥብ 45 ኪሎ ሜትር ባለ 0 ነጥብ 4 ኪሎ ቮልት የዝቅተኛ መስመር ማሻሻያ፣ ግንባታና ነባር መስመሮችን የማንሳት፣ የ32 ነባር ዲስትሪቢዩሽን ትራንስፎርመሮች ማሻሻያ ስራ፣ የ47 አዳዲስ ዲስትሪቢዩሽን ትራንስፎርመሮች የመትከል እና የ9 ሺህ 229 ኮንክሪት ምሰሶ ተከላ ስራ ለማከናወን ታቅዶ በአሁኑ ስዓት ከውጪ አገር የሚገቡ የግንባታ እቃዎች አቅርቦት 92 በመቶ ተከናውኗል ተብሏል፡፡
በአገር ውስጥ ከሚመረቱ የኮንክሪት ምሰሶ አቅርቦት አንጻር፥ 7 ሺህ 973 (የኮንትራቱን 94 ከመቶ) የኮንክሪት ምሰሶዎች ተመርተው የጥራት ፍተሻውን ካለፉ በኋላ ወደ ሳይት መጓጓዛቸው ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም 6 ሺህ 559 (የኮንትራቱን 73 ከመቶ) የዝቅተኛና የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ኮንክሪት ምሰሶዎችን የመትከል ስራ መከናወኑም ተመላክቷል፡፡
በሎት 3 ጎንደርና አዲግራት ከተሞች ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የማሻሻያ ስራ የ242 ነጥብ 63 ኪሎ ሜትር ባለ 15 ኪሎ ቮልት የመካከለኛ መስመር ማሻሻያ፣ ግንባታና ነባር መስመሮችን የማንሳት፣ የ127 ነጥብ 86 ኪሎሜትር ባለ 0 ነጥብ 4 ኪሎ ቮልት የዝቅተኛ መስመር ማሻሻያ፣ ግንባታና ነባር መስመሮችን የማንሳት፣ የ51 ነባር የዲስትሪቢዩሽን ትራንስፎርመሮች ማሻሻያ ስራ፣ የ46 አዲስ የዲስትሪቢዩሽን ትራንስፎርመር ተከላ ስራ እና የ10 ሺህ 221 የኮንክሪት ምሰሶ ተከላ ስራን የሚሽፍን ነው ተብሏል፡፡
በጎንደርና አዲግራት ከተሞች ለማከናወን ከታቀደው የማሻሻያ ስራዎች መካከል የዲዛይን ስራዎችን ከማከናወን ጀምሮ አስፈላጊ የሆኑና ከውጪ አገር ከሚቀርቡ የግንባታ እቃዎች አቅርቦት 95 በመቶ መከናወኑን የኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡
የአገር ውስጥ የምሰሶ አቅርቦት በጎንደር ብቻ 4 ሺህ 319 የኮንክሪት ምሰሶዎች (የኮንትራቱን 34 ከመቶ) ወደ ጎንደር ከተማ መድረሱ እና በዚሁ ሎት የ2 ሺህ 65 (የኮንትራቱን 21 ከመቶ) ኮንክሪት ምሰሶ ተከላ ስራ እንዲሁም የ12 ነጥብ 49 ኪሎ ሜትር ዝቅተኛ ቮልቴጅ መስመር ዝርጋታ ስራ ተከናውኗል፡፡
የአዲግራት ከተማ የማሻሻያ ስራ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ስራው ያልተከናወነ በመሆኑ÷ በምትኩ የኮምቦልቻ ከተማ የማሻሻያና ማስፋፊያ ሥራ ለማከናወን ከተቋራጩ ጋር ስምምነት ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡
በተጨማሪም በ13 ከተሞች 150 ሺህ አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል፣ የቆጣሪ እና ሰርኪውት ብሬከር ግዢ መከናወኑ እንዲሁም ኬብል እና ተዘማጅ እቃዎች አቅርቦት ግዥ በመከናወን ላይ ነው ተብሏል፡፡
በፕሮጀክቱ ሰብስቴሽኖች እና ትራንስፎርመር ጋር የሚገጠሙ የኃይል መከታተያና መቆጣጠሪያ እንዲሁም መስመር ሳይቋረጥ ለመጠገን የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን ግዢ በሂደት ላይ መሆኑን ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ 80 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የሚደረግበት ሲሆን የፕሮጀክቱ የገንዘብ ምንጭም የዓለም ባንክ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈጻፀም 69 በመቶ የደረሰ ሲሆን÷ በዚህ በጀት አመት መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.