Fana: At a Speed of Life!

ከሃይማኖት ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ  ግጭቶችና አለመግባባቶች  የግለሰቦች እንጂ የሃይማኖት መሰረት የላቸውም – የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሁኑ ወቅት ከሀይማኖት ተያይዘው በሀገሪቱ የሚስተዋሉ  ግጭቶችና አለመግባባቶች የግለሰቦች እንጂ የሃይማኖት መሰረት የላቸውም ሲል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ፡፡

“የማህበረሰብን ሰላምና አብሮነት ለማጠናከር የሃይማኖቶች የጋራ እሴቶች ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በጎንደር ከተማ ውይይት እያካሄደ ነው፡፡

የጉባኤው ዋና ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ጉባኤው ወቅታዊ የሃገሪቱን ፈተናዎች ለማስወገድና የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ለመወያየት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚታዩ ግጭቶችና አለመግባባቶችም የግለሰቦች እንጂ የሃይማኖት መሰረት የሌላቸው ናቸው ብለዋል።

ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የሚነሱ ጠላቶቻችን የእምነትና ማንነት ደካማ ጎናችንን ምክንያት እያደረጉ ነው ያሉት ዋና ፀሐፊው፥  የግጭት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን የሃይማኖት ተቋማቱ ቀድመው ሊከላከሉ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በሰላም ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ አምባሳደር እሸቱ ደሴ እንደገለጹት፥ በሀገሪቱ ታሪክ ሃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ እንጂ የሃይማኖት ግጭቶች አልነበሩም፡፡

ተከባብሮና ተሳስቦ ለመኖርም ተቋማቱ እያበረከቱ ያለውን ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም፥  ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው የሚጀመሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች በቶሎ ከመቋጨት ይልቅ የመስፋፋት እድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ የእምነት አባቶች ከስር ከስር ማህበረሰቡን ማስተማርና ማረም እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

በሙሉጌታ ደሴ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.