Fana: At a Speed of Life!

ከሊፋ ሃፍጣር በፋይዝ አል ሳራጅ የተጠራውን የተኩስ አቁም እንደማይቀበሉ አስታወቁ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 18 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) መቀመጫውን በምስራቃዊ ሊቢያ ያደረገው የከሊፋ ሃፍጣር ሃይል በጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዝ አል ሳራጅ የተጠራውን የተኩስ አቁም እንደማይቀበለው አስታወቀ፡፡

ራሱን የሊቢያ ብሄራዊ ወታደራዊ ሃይል ብሎ የሚጠራው ቡድን ቃል አቀባይ አህመድ ሚስማሪ ባለፈው ዓርብ የተጠራው የተኩስ አቁም “ለሚዲያ ፍጆታ” የሚውል በሚል አጣጥለውታል፡፡

ቃል አቀባዩ የፋይዝ አል ሳራጅ አስተዳደር ጥቃት ለመፈጸም በሚያስችለው መልኩ በሲርጥ አካባቢ ሃይሉን እያደራጀና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ወደስፍራው እየላከ ነው በማለት ተችተዋል፡፡

እውነተኛ የተኩስ አቁም ከተፈለገም በመንግስታቱ ድርጅት እውቅና የተሰጠው የአል ሳራጅ አስተዳደር ወታደሮቹን ከአካባቢው ማራቅ ይገባዋልም ነው ያሉት፡፡

ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ጥሪው ከሚዲያ ፍጆታነት የዘለለ ሚና እንደማይኖረውና የሚቃጣባቸውን ጥቃት ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የአል ሳራጅ መንግስት ባለፈው ዓርብ በመላው ሊቢያ የተኩስ አቁም ማድረጉን በመግለጽ ታጣቂ ሃይሎች የተኩስ አቁሙን እንዲተገብሩ ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡

ከዚህ ባለፈም ሲርጥን ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ማድረግና በመጭው መጋቢት ወር አካባቢያዊና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይካሄድ ዘንድ ጥሪ ማቅረቡም ይታወሳል፡፡

ምንጭ፣ አልጀዚራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.