Fana: At a Speed of Life!

ከልጅ እጅ ጠብቀው፥ ከሚያገኙት ቀንሰው ለወገን ጦር ድጋፍ የቸሩ እናት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) ወ/ሮ ውዴ በለጠ ይባላሉ። ነዋሪነታቸው ጎንደር ከተማ ቀበሌ 17 ነው። ሀገሬ በችግር ውስጥ ሆና እኔ በድሎት አልኖርም በማለት ልጆቻቸው ለቀለብ ብለው ከሚሰጧቸው ጥቂት ገንዘብ እየቆጠቡ ለሰራዊት አባላት በግላቸው ስንቅ አዘጋጅተው አቅርበዋል።

ወ/ሮ ውዴ የልጆቻቸውን እጅ ጠብቀው የሚኖሩ እናት ቢሆኑም ለህልውና ዘመቻ የሀገርን ክብርና የወገንን ህልውና ለማስጠበቅ ግንባር ለተሰለፉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የአማራ ልዩ ሀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ ይሁንልኝ ሲሉ 3 ኩንታል በሶ አዘጋጅተው ድጋፍ አበርክተዋል።

ግለሰቧ “ከዚህ በፊትም ልጆቼ በቻሉት አቅም ግንባር ለዘመቱ ወገኖቻቸው ድጋፍ አድርገዋል” ይላሉ። “አሁን ደግሞ የኔ ተራ ነው፤ ከወር ቀለቤ እየቀነስኩ በሰበሰብኳትና ልጆቼ በሰጡኝ ጥቂት ገንዘብ ይህንን አድርጌያለሁ” አሉ።
እኔ በሰላም ወጥቼ እንዲገባ እነሱ ህይወታቸውን አሳልፈው የሰጡኝ ዘማቾች ልጆቼና ወንድሞቼ ናቸውና ወደፊትም ባለኝ አቅም ሁሉ ድጋፌን እቀጥላለሁ ነው የሚሉት።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈፀመውን ዓይነት አረመኔያዊ ድርጊት “ በህይወት ዘመኔ አይቼም ሰምቼም አላውቅም” የሚሉት ወ/ሮ ውዴ ፥ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ተረባርቦ ሊያስወግደውና የሀገሩን ሰላም ሊጠብቅ ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አቅርበዋል።

በሙሉጌታ ደሴ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.