Fana: At a Speed of Life!

ከመስከረም 30 ቀን በኋላ የፌደራል መንግስት ህጋዊነት እስከምን ድረስ ነው?

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፖለቲካል ሳይንስ ምሁራን ከመስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም በኋላ የፌደራል መንግስት ህጋዊነት እስከምን ድረስ ነው ለሚለው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የዘርፉ ምሁራን የፌደራል መንግስት በህገ መንግስት ትርጉም ህጋዊ ስልጣኑን በማራዘሙ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ሀገር በማስተዳደር ህጋዊ መንግስት ሆኖ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
ምርጫ የተራዘመበት መንገድም ህግና ህጋዊነትን የተከተለ አካሄድ መሆኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም መምህር ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ ተናግረዋል ።
ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም ኋሃላ መንግስት የለም የሚሉ ሀይሎች በህገ ወጥ መንገድ ያከናወኑትን ምርጫ ህጋዊ ለማስመሰል የሚያደርጉትን ጥረት ተራ ጨዋታ ነው ብለውታል ።
የኮሮና ቫይረስ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ እንዲራዘም ገፊ ምክንያት ሆኖ ፤ መንግስትን የህገ መንግስት ትርጉም እንዲያካሂድ ማድረጉን ያስታውሳሉ ።
ይህ የህገ መንግስት ትርጉም ደግሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን፣ የስራ አስፈጻሚውንና ተርጓሚውን ህጋዊነት ከራሱ ህገ መንግስት ምሰሶዎች ጋር በታረቀ እና በተናበበ መልኩ መፍትሄ ያስቀመጠ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስትም ህግና ህገ መንግስታዊ በሆነ መልኩ ምርጫን አራዝሞ ከመስከረም 30 ቀን በኋላም ቢሆን ሀገር የማስተዳደር ልእልናን በህግና በህግ ብቻ የተጎናጸፈ መሆኑንም ያስረዳሉ።
ህገ መንግስቱ ለክልሎች ከሚሰጠው ስልጣን የወጡ የራሳቸውን ምርጫ ያካሄዱ አካላት ድርጊታቸው ህገ ወጥ እንደመሆኑ ህጋዊ የማድረግ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተዋል ነው የሚሉት ።
ለዚህ የራስን ምርጫ ህጋዊ እውቅና ለማግኘት የፌደራል መንግስቱ የሄደበትን ህገ መንግስታዊ መንገዶች ማጣጣል ተራ የሚጠበቅ ፕሮፓጋንዳ በማለት ገልፀውታል።
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ዶክተር ውብ እግዜር ፈረደ ዳግሞ ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ ምርጫን ያራዘመውና ፤የህገ መንግስት ትርጓሜን ያከናወነው መንግስት ከመስከረም 30 ቀን በኋላ ህጋዊ ሆኖ ይቀጥላል ነው የሚሉት ።
በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶክተር አየነው ብርሃኑ ደግሞ ስለ ህገ መንግስት እና ህጋዊነት ዲስኩር ላይ እየደከመ ያለው አካል ለመሆኑ ዳግም ወደ ስልጣን የመውጣት ጉጉቱ ከሀሳብ ልእልና የመነጨና ለሀገራዊ ደህንነት የተጨነቀ ነው ወይ ሲሉ ይጠይቃሉ።
ምሁሩ ለጥያቄያቸው ምላሽ ላለፉት 27 አመታት የህገ መንግስት ጥሰት ልምምዱን ዳግም በህገ ወጥ መንገድ ወደ ስልጣን ዙፋኑ ለመውጣት የሚያደርገው ሴራ መሆኑንም ያስቀምጣሉ ።
ይህ ሂደት ህግን ያልተከተለ ስልጣን ላይ ካለው መንግስት ይልቅ ህጋዊና ተቀባይ ስርአት ነው ብለዋል ።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ የነበራቸው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራኑ አሁንም ቢሆን በህጋዊ መንገድ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ለማስጠበቅ ሊሰራ እንደሚገባው አጽንኦት ሰጥተዋል።
ህግና ስርአትን የማስከበር ግዴታውን መወጣቱን እንዲያጠናክር በመምከርም÷ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች የመወያየት ልምዱ ሊቀጥል ፤ በሀሳብ የበላይነት የማመን የዴሞክራሲ አካሄዱም ሊጠናከር ይገባልም ነው ያሉት።
በሀይለየሱስ መኮንን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.