Fana: At a Speed of Life!

ከመቅደላ ተዘርፈው የተወሰዱ የኢትዮጵያ ቅርሶች ከጨረታ እንዲታገዱ ተደረገ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ቅርሶቹ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የእንግሊዝ ሜጀር ጄኔራል ዊሊያም አርቦትኖት የተዘረፉ ጥንታዊ የብራና የጸሎት መጽሃፍ፣ ከቆዳ የተሰራ የመጽሃፍ መያዣ ከእነመስቀሉ እንዲሁም ከቀንድ የተሰሩ በብር የተለበጡ ጥንታዊ ዋንጫዎች እንደሆኑ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል ፡፡

እነዚህ ከኢትዮጵያ ተዘርፈው የመጡት ቅርሶች ባስቢ በተባለ ለንደን በሚገኝ ታዋቂ የቅርስ አጫራች ኩባንያ በኩል ከፍተኛ ተጫራቾች በሚገኙበት በዛሬው እለት ለሽያጭ ሊቀርቡ እንደነበርም ኤምባሲው ገልጿል፡፡

ኤምባሲው ስለ ጉዳዩ አስቀድሞ በደረሰው መረጃ ቅርሶቹ የኢትዮጵያ ንብረት መሆናችውን በመግለፅ እና ለባለቤቱ መመለስ እንዳለባቸው በማሳመን በለንደን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለመመለስ ስምምነት ተደርሷልም ነው ያለው፡፡

ቅርሶቹ ለሃገር መንፈሳዊ ፣ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ሲሆን ሌሎች በዘረፋ የተወሰዱ ቅርሶችን በዚህ መልክ በድርድር ለማስመለስ አስተዋፅኦ እንዳለውም አመላክቷል፡፡

በቀጣይነት በእንግሊዝ ከመቅደላ የተዘረፉ ቅርሶች እንዲመለሱ ከፍተኛ ድርድሮች እየተደረጉ እንደሆነ መገለጹን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

በኢትዮጵያና በእንግሊዝ ታሪካዊ የጋራ ግንኙነት ላይ መቅደላ የፈጠረውን መጥፎ አጋጣሚ በአዎንታዊነት ለማደስ እነዚህ በህገወጥ መንገድ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉ ፋይዳው ከፍተኛ ነው ብሏል፡፡

ከሁለት አመት በፊት የአፄ ቴዎድሮስ ሹሩባ ከለንደን ወደ ሀገሩ በክብር እንዲመለስ መድረጉ ይታወሳል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.