Fana: At a Speed of Life!

ከማላዊ ወደ ሞዛምቢክ ሲጓዝ በነበረ ከባድ መኪና ውስጥ 64 ኢትዮጵያውያን መሞታቸው ተረጋገጠ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው የኢፌዴሪ ኤምባሲ ባገኘው መረጃ መሰረት ከማላዊ ወደ ሞዛምቢክ ሲጓዝ በነበረ የጭነት መኪና ውስጥ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ህይወት ማለፉን እና የሟቾቹን ብዛት እና መሰል ዝርዝር መረጃዎችን በተመለከተ በቀጣይ እንደሚያሳውቅ ትናንት ባወጣው የሀዘን መግለጫ መግለጹ ይታወሳል።

በዚሁ መሰረት በእቃ ጫኝ ከባድ ተሽከርካሪ ኮንቴነር ውስጥ ከማላዊ ወደ ሞዛቢክ ድንበር በመጓዝ ላይ ከነበሩ 78 ኢትዮጵያውያን ውስጥ 64ቱ በአየር እጥረት ምክንያት ታፍነው መሞታቸውን እና 14ቱ በህይወት መትረፋቸውን ከኤምባሲያችን ባገኘነው ተጨማሪ መረጃ አረጋግጠናል ብሏል።

ሁሉም ተጓዞች ህጋዊ የጉዞ ሰነድ ያልነበራቸው መሆኑን እና ማንነታቸውን በተመለከተ በህይወት ከተረፉት ኢትዮጵያውያን ማረጋጋጥ መቻሉንም ኤምባሲው ማሳወቁን ነው የጠቆመው።

አደጋው የደረሰበት ቴቴ በመባል የሚታወቀው አካባቢ ከተለያዩ ሃገራት በህገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች በመደለል ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ ሙከራ የሚያደርጉ ሰዎች የሚገኙበት የታወቀ መተላለፊያ ቦታ መሆኑንም ኤምባሲው እንዳሳወቀው ገልጿል።

በህይወት የተረፉት 14ቱ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ሰዓት ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው የኢፌዴሪ ኤምባሲ፣ በሞዛምቢክ መንግስት፣ ሞዛምቢክ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የስደተኞች ፅህፈት ቤት እና ሞዛምቢክ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አባላት በኩል እርዳታ እና ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝና አስፈላጊው የጉዞ ሰነድ ከተመቻቸላቸው በኋላ በቅርቡ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያውያን ላይ በደረሰው አሰቃቂ አደጋ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን በድጋሚ በመግለፅ ለሟች ቤተሰቦች እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.