Fana: At a Speed of Life!

ከሰላማዊ ዜጎች ግድያና ከጾታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ በ53 የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ከሰላማዊ ዜጎች ግድያና ከጾታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ በ53 የሃገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ክስ መመስረቱን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ።

በማይካድራ ከንጹሃን ግድያ ጋር በተያያዘ 200 ሰዎች መለየታቸው እና ከእነዚህም ወስጥ 23ቱ በቁጥጥር ስር ውለው ክስ እንደተመሰረተባቸውም ይፋ አድርጓል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ጋር በመሆን በሃገር ውስጥ ለሚገኙ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ በዚህ ወቅት በትግራይ ክልል ተፈጸሙ የተባሉ ወንጀሎችን በማጣራት ረገድ የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

በምርመራው የአሸባሪው ህወሃት ስራ አስፈጻሚ አባላት የታጠቁ ወታደሮችን በማደራጀት የሰሜን እዝን ከማጥቃት ጀምሮ የህገ መንግስት ጥሰትን በተለያዩ አካባቢዎች የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲፈጸም ጥረት ማድረጋቸው ተረጋግጧል ብለዋል።

በተጨማሪም ይህ ኃይል በፌዴራል ተቋማት የሚገኙ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ላይ ጥቃት ፈጽሟል፤ ተቋማቱንም አውድሟል ነው ያሉት።

በወንጀሉ የተጠረጠሩ የተወሰኑ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ሌሎችን የማደኑ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተለያዩ ጥፋቶች ላይ ተሰማርተው የተገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተጠያቂ እንደሚሆኑ ቀደም ሲል መግለጻቸው ይታወሳል።

በዚህም መሰረት ክልሉ ከሰላማዊ ዜጎች ግድያ ጋር በተያያዘ 28 እንዲሁም ከጾታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ 25 የሃገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ክስ መመስረቱንም ጠቁመዋል።

እስካሁን ባለው ሂደትም በክልሉ ከ100 በላይ ሰላማዊ ዜጎች ህይወታቸው ማለፉን ነው ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ የተናገሩት።

በማይካድራ በሰላማዊ ዜጎች ላይ በተፈጸመ ጭፍጨፋ ደግሞ በርካቶች መሞታቸውንና ለከፋ አካላዊ ጉዳት መዳረጋቸውን አንስተዋል።

ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ ‘እጃቸው አለበት’ ተብለው 200 ሰዎች መለየታቸውንና ከእነዚህ ውስጥ 23ቱ በቁጥጥር ስር ውለው ክስ ተመስርቶባቸዋል ነው ያሉት።

የፍርድ ሂደታቸውም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እየተከናወነ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በማይካድራ የሰላማዊ ዜጎች እልቂት እጃቸው አለበት ተብለው ከተለዩ ሰዎች መካከል በርካቶች ወደ ሱዳን መሸሻቸውንም ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ገልጸዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.