Fana: At a Speed of Life!

ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የተወሰነባቸው የተመድ ሠራተኞች የህወሓትን ሴራ ሲያስፈጽሙ ነበር- አምባሳደር ታዬ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የተወሰነባቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች የተቋማቸውን የሙያ ሥነ ምግባር በመጣስ ፖለቲካዊ አቋም ይዘው የአሸባሪውን የህወሓት ቡድን ሴራ ሲደግፉና ሲፈጽሙ እንደነበር አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ፡፡
በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ለፀጥታው ምክር ቤት ትናንት በሰጡት ማብራሪያ፥ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የታዘዙት የተመድ ሠራተኞች የራሱን የድርጅቱን ሕግና የሙያ ሥነ ምግባር በመጣስ ለወራት ያህል የህወሓትን ሴራ በመደገፍ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አመልክተዋል፡፡
ከአገር እንዲወጡ የተወሰነባቸው የተመድ ሠራተኞች የህወሓትን አመራሮችና የቡድኑን አባላት ሤራ ሲያስፈፅሙ እንደነበር አስረድተዋል።
በህወሃት ሤራ የተጠለፉት እነዚህ የተመድ ሠራተኞች በጦርነቱ ምክንያት አያሌ ንፁሃን ሰዎች ተጎድተዋል፣ ተገድለዋልም የሚል ሀሰተኛ ምስል ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሲያስተላልፉ እንደነበር ጠቅሰዋል።
የአሸባሪውን ቡድን አባላት ለማስመለጥም ሙከራ ሲያደርጉ ቆይተዋል፣ በራሳቸው አባባልም በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ “ዳርፉርን እናደርገዋለን ” ብለው አልመው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አንስተዋል።
ሠራተኞቹ የተመደቡበትን ሰብዓዊ አገልግሎት በገለልተኛነት፣ በሰብዓዊነትና በነጻነት መሥራ ሲገባቸው፥ ሥራቸውን ትተው በህወሓት ሴራ በመጠለፍ ሀሰተኛና የተዛባ መረጃ በማስተላለፍ፣ የጦር መሣሪያ በማቀበልና በሌሎች የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመሳተፍ ለአሸባሪው ቡድን ሲሰሩ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
በትግራይ ክልል ውስጥ በረሃብ ያልሞቱ ሰዎችን እንደሞቱ በመቁጠር የተረጂዎችን ቁጥር በሚሊየን በመጨመርና በሌሎች ለቡድኑ ወገንተኝነታቸውን በሚያረጋግጡ ተግባራት ተሳትፈዋል ብለዋል፡፡
ለአብነትም በትግራይ ክልል 2 ነጥ 8 ሚሊየን ተረጂዎች እንዳሉ በአዲስ አበባው የተመድ የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የተላለፈ ሪፖርት 3 ነጥብ 8 ሚሊየን እንደሆነ ተደርጎ መተላለፉን አንስተዋል።
ሪፖርቱ በዚህ ደረጃ ተጋኖ የቀረበበት ሮም በሚገኙ የህወሃት ተላላኪዎች አማካይነት መሆኑን የገለጹት አምባሳደረ ታዬ፥ ይህ የሆነበት ምክንያትም ችግር ላይ ለሚገኙ የክልሉ ዜጎቻችን በማሰብ ሳይሆን የትህነግ የፖለቲካ ሴራ አካል በመሆኑ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በተመድ ውስጥ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሠራተኞች ሥራቸውን በአግባቡ እንደሚሠሩ ትገነዘባለች ያሉት አምባሳደር ታዬ÷ ለኢትዮጵያ “አስፈላጊ ሰዎች አይደሉም” ተብለው ከአገር እንዲወጡ የተወሰነባቸው ግለሰቦች፥ የገቡትን ቃል ያጠፉ፣ ሙዊ ሥነ ምግባራቸውንና የሰብዓዊ አገልግሎትን መርህ የጣሱ ናቸው ብለዋል፡፡
ስለሆነም ኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት የሚሠሩ ሠራተኞችን ተግባር የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራዋን አጠናክራ በመቀጠል ሙሉ ሉዓላዊ መብቷን እንደምትጠቀም ገልጸዋል።
ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን አክብረው ለሚሠሩት የተመድ ሠራተኞችና ኃላፊዎች አክብሮት የምትሰጥ መሆንዋንም አምባሳደር ታዬ አስታውቀዋል፡፡
በተመድ የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ የሚሠሩ ሠራተኞች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ጉዳዩ በትዕግስት ሲታይ የቆየ መሆኑን ጠቁመው÷ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አማካይነት ለተመድ ደብዳቤ ተጽፎ ምክር እንዲሰጣቸው የተጠየቀ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የተወሰነባቸው የተመድ ሠራተኞችና ሃላፊዎች ሀሰተኛ መረጃችን በማሰራጨት መሰማራታቸውን ጠቁመው ፥ በአንድ ሌሊት ብቻ የ1 ሚሊየን ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ነው ብለው ሀሰተኛ ሪፖርት አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ሰራዊት ወንጀል ተፈፅሟል የሚል ሀሰተኛ መረጃ በማውጣትም ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት እንዲቀርብ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በቀድሞ የተመድ የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊም 152 ኢትዮጵያውያን በምግብ እጥረት ምክንያት ሞተዋል ብለው የሀሰት መረጃ እንዲዘጋጅና ሪፖርት እንዲላክ አድርገዋል፥ እንዲህ ዓይነት ክስተት በፍፁም አልነበረም ነው ያሉት አምባሳደር ታዬ፡፡
ከ 2 ሣምንታት በፊትም እንዲሁ 12 ሰዎች በረሃብ ምክንያት በዕርዳታ መስጫ ካምፕ ውስጥ ሞቱ ብለው ሪፖርት አድርገዋል፡፡
ነገር ግን የእርዳታ ድርጅቱ ባልደረባ የሆኑ ሰዎች ቀርበው ውንጀላው ሃሰት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የተጠቀሱት የተመድ ሠራተኞች ከኃላፊነታቸው ውጪ “የማጣራት ስራ ለመስራት” በሚል ሰበብ የህወሓትን አጀንዳ ለማስፈፀም ሲጥሩ እና መንግስትን የሚወነጅሉ የሀሰት መረጃዎችን ሲያሰራጩ እንደነበር አብራርተዋል፡፡
የተመድ ኤጀንሲዎች ዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች ወደ ቦታው ከመድረሳቸው በፊት በህወሓት ታጠቂዎች ሲፈፀሙ የነበሩ ፆታዊ ጥቃቶችን ለማጋለጥ ካለመሞከራቸውም በላይ በህወሓት ታጠቂዎች እንዲደፈሩ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የመንግስት ሃይሎችን ለመወንጀል ጥረት አድርገዋል ብለዋል።
እነዚህ በሰብዓዊ ድጋፍ ስም የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች፥ የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል ከትግራይ ክልል ለቆ ሲወጣ፤ ከህወሓት ቡድን ጋር በመሆን በድል አድራጊነት ስሜት ደስታቸውን ሲገልጹና ሲጨፍሩ የሚያሳዩ ማስረጃዎች እንዳሉም ነው ያመለከቱት፡፡
በተጨማሪም እነዚህ የተመድ ሠራተኞች የሰብዓዊ አገልግሎታቸውን ወደ ጎን ትተው የአክቲቪዝም ስራ ሲሰሩ እንደነበርና ለአሸባሪው ቡድን የምግብ፣ የመድሃኒት ፣ የመገናኛ አገልግሎት እና የመሳሰሉትን እርዳታዎች ሲያደርጉለት እንደቆዩ ገልጸዋል ፡፡
በሳኡዲ አረቢያ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ውስጥ ብሔርን መሠረት ባደረገ መልኩ እየለዩ ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ሁኔታዎችን ሲያመቻቹ እንደነበርም ጠቁመው፥ ተመላሽ የትግራይ ተወላጆችን በሌላ ሶስተኛ ሀገር እንዲሰፍሩ በማድረግ ወታደራዊ ስልጠና በመስጠትና ለውጊያ ዝግጁ በማድረግ በኩልም አስተዋጽኦ ነበራቸው ብለዋል።
አብዛኞቹ የተባበሩት መንግስታት ሠራተኞች የሙያ ሥነ ምግባራቸውን አክብረው ሥራቸውን የሚሰሩ መሆናቸውን ገልጸው፥ ለእነዚህ ሠራተኞችና ተመድ ለተቸገሩ ዜጎቻችን ለሚሰጠው ሰብዓዊ ድጋፍ ኢትዮጵያ ትልቅ አክብሮት እንዳላት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በክብርና በእኩልነት መርህ ከሚመመለከቷት ወዳጆቿ ጋር ተባብራ ለመስራት ቁርጠኛ አቋም እንዳላት የገለጹት አምባሳደር ታዬ፥ የሙያ ሥነ ምግባራቸውንና የሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎታቸውን በአግባቡ የሚያከናውኑ የተመድ ሠራተኞችን ለመቀበል በሯ ክፍት መሆኑንም አመልክተዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
26
People Reached
1,388
Engagements
Boost Post
587
12 Comments
47 Shares
Like

Comment
Share
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.