Fana: At a Speed of Life!

ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በደህንነት ስጋት የወጡ ከ35 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመለስ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 7 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በደህንነት ስጋት የወጡ ከ35 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተፈጠሩ ችግሮችን እንዲመረምር የተቋቋመው ኮሚቴ በ22 ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ያደረገውን የክትትልና የድጋፍ ሪፖርት አቅርቧል።

ኮሚቴው በቅኝቱ የተማሪዎችና ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን መዳሰሱ ተገልጿል።

ባደረገው ቅኝትም ተማሪዎች ሳያውቁም ይሁን አውቀውት ከብሄርተኝነት ጋር ተያይዞ ጎራ የመለየትና በአንድ ቡድን በመሰባሰብ ጽንፍ የመያዝ አዝማሚያ ይታይባቸዋል ብሏል።

የዩኒቨርሲቲ አስተዳደር አለመናበብ፣ የአመራር ክፍተት፣ ተገቢውን እርምጃ አለመውሰድ፣ የክትትልና ድጋፍ ማነስ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አቅራቢያ ተማሪዎችን ለሱስ የሚዳርጉ የንግድ ቤቶች መበራከት በቅኝት ወቅት የተስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውም ተጠቅሷል።

ከዚህ ባለፈም የፖለቲካ አመራሮች ለዩኒቨርሲቲዎች የሰላም እጦት ትልቅ ሚና ተጫውተዋልም ነው የተባለው።

ኮሚቴው አዋጅና ደንቦች በወጥነት ቢተገበሩ፣ የተማሪዎች አመዳደብ ስብጥር ቢኖረው፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የእውቀት ክህሎት ክፍተትን መቅረፍ፣ በቴክኖሎጅ የታገዝ የጥበቃ ቢተገበር፣ በአካል ተገኝቶ መደገፍ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ከማህበረሰቡ ጋር ማቀራረብ እና ጠንካራ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ ቢቻል የሚል ምክረ ሃሳብም አቅርቧል።

በአማራ እና ኦሮሚያ ክልልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የተደረገው የኮሚቴው ምርመራ፥ 85 በመቶ ውጤታማ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተፈጠሩ ችግሮች ጋር ተያይዞ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም ተናግረዋል።

በዚህም 640 ተማሪዎች፣ 40 መምህራን እና ከ240 በላይ የአስተዳደር ሰራተኞች ላይ የኮሚቴውን ምክረ ሃሳብ መሰረት አድርጎ እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት።

በተስፋዬ ከበደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.