Fana: At a Speed of Life!

ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተገናኘ ወደ ቻይና በረራ ማቆም ዋስትና አይሰጥም – አቶ ተወልደ ገ/ማርያም

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተገናኘ ወደ ቻይና በረራ ማቆሙ ዋስትና እንደማይሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ገለፁ።

ዋና ስራ አስፈጻሚው አየር መንገዱ ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተገናኘ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ እንደማያቋርጥም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

አየር መንገዱ በርካታ ዓለም አቀፍ በረራዎችን እንደማድረጉ ወደ ቻይና ብቻ በረራ ማቆም ዋስትና እንደማይሆንም ነው የተናገሩት።

ወደ ቻይና የሚደረገው በረራ ቢቆም እንኳን የቫይረሱ ተጠርጣሪዎች ወዳሉባቸው ሀገራት በረራ እንደማድረጉ ከስጋቱ ነጻ መሆን አይቻልም ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፥ አየር መንገዱ በትራንዚት ከሌሎች መዳረሻዎቹ በርካታ ቻይናውያንን እንደሚያጓጉዝም ጠቅሰዋል።

መፍትሄው ለደንበኞች እና ሰራተኞች ጤንነት ጥንቃቄ ማድረግ ብቻ ነው ሲሉም አስረድተዋል።

በመሆኑም ቫይረሱን ለመከላከል አየር መንገዱ በመዳረሻ ሀገራትም ሆነ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከፍተኛ የቁጥጥር ስራ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አያይዘውም የዓለም ጤና ድርጅት የጉዞ እገዳ ማድረግ እንደማይገባ ያቀረበውን ምክር እናከብራለን ብለዋል።

70 በመቶ ቻይናውያን መንገደኞች በትራንዚት አዲስ አበባን እንደሚረግጡ ያነሱት አቶ ተወልደ፥ በማግለል መፍትሄ እንደማይመጣ መረዳት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደምም የኢቦላ ወረርሽኝ ባጋጠመ ጊዜ አየር መንገዱ የሚያደርገውን በረራ አለማቆሙን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት 35 በረራ ወደ ቻይና ያደርጋል።

የብሪታኒያ አየር መንገድ ወደ ቻይና በረራ ቢያቆምም የቻይና አየር መንገድ ግን በቀን በርካታ በረራዎችን ወደ ብሪታንያ እያደረገ ይገኛል።

በሀይለየሱስ መኮንን

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.