Fana: At a Speed of Life!

ከውጭ ሀገር የተላከላችሁን ስጦታ የቀረጥና ማጓጓዣ ከፍላቹ ውሰዱ በማለት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ያጭበረበሩ 13 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ናይጄሪያ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ለህገወጥ ማታለል ስራ ተደራጅተው በማህበራዊ ድረገጽ በማታለል ወንጀል ላይ ተሰማርተው የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

ግለሰቦቹ በዋናነት ሴቶችን በመተዋወቅና በማግባባት ከውጭ ሀገር የተለያዩ ስጦታ ልከናል ቀረጥና ማጓጓዣ በባንክ ከፍላቹ ውሰዱ በማለት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ አጭበርብረው በወስደው ተሰውረው የነበሩ ናቸው።

በአሁኑ ወቅትምን በቁጥጥር ስር የዋሉት 13 ግለሰቦች ጉዳያቸው በህግ የተያዘ መሆኑን ያስታወቀው የፌደራል ፖሊስ፥ ሌሎችም በተመሳሳይ ተግባር የተሰማሩ መኖራቸው ጠቁሟል።

በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የፋይናንስና ንግድ ጉዳዮች ወንጀል ምርመራ ዳይሬክተር ኮማንደር ብርሀኑ አበበ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮሮፖሬት እንደተናገሩት፥ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ሰዎችን በተለይም ሴቶችን በማህበራዊ ድረገጽ በመተዋወቅ ውጭ እንደሚኖሩ፣ ከውጭ እርዳታ እንደሚያደርጉና የውጭ ሀገር ጉዞ እድል እንደሚሰጡ በማግባባት ያሳምናሉ ብለዋል።

ይህን እምነታቸውን ተጠቅመው ከውጭ ሀገር የተለያዩ ስጦታዎችን ልከንላችኋል በማለት የተለያዩ የማታለል ተግባራትን እንደሚፈፅሙም ነው ኮማንደር ብርሃኑ የገለፁት።

በዚሁ ወቅትም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ቡድኖች ደግሞ በስልካቸው በመደወል የተላከላቸውን እቃ በባንክ ሂሳብ የማጓጓዣ እና ቀረጥ ከፍላችሁ ውሰዱ በማለት እደሚያታልሉ ገልጸዋል።

በዚህ መንገድም ገንዘቡ ባንክ እዲገባ በማድረግ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ወስደው ተሰውረው የነበረ ሲሆን፥ በተደረገ በክትትል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል።

የመታለል ወንጀል ደርሶብናል ያሉ 70 ግለሰቦች ቀርበው ማሳወቃቸውንም ነው ኮማንደር ብርሃኑ የተናገሩት።

አሁንም ሌሎች በዚህ ተግባር የተሰማሩ ግለሰቦች መኖራቸውን የጠቆሙት ኮማንደሩ ፥ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡም በመሰል የማታለል ወንጀል ከተሰማሩ አካላት ራሱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.