Fana: At a Speed of Life!

ከፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አስተባባሪዎች ጋር በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ ላይ ውይይት ተደረገ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 15፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አስተባባሪዎች ጋር በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮችና ከቡድኑ ጋር አብሮ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት አደረጉ።

አምባሳደር ዲና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እንዲሁም በኢትዮጵያ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ መንግሥት እየሰራ የሚገኘው የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴን በሚመለከት ገለጻ አድርገዋል።

አያይዘውም ባጋጠመው ሃገራዊ ሁኔታ በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስገንዘብ፣ ለጎረቤት ሃገራት ህዝቦችና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኖች ሁኔታውን በማስረዳት ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ በመሆኑ ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ቡድኑ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርግ የጠየቁ ሲሆን፤ በመንግሥት በኩል በሁኔታው ላይ ያለውን መረጃ ለቡድን በመስጠትና ሰውን በማስተባበር እንደሚሰራ ገልፀዋል።

የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አስተባባሪ አባላት በበኩላቸው አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ የሁሉም አካላትና ሃገር ወዳድ ዜጎች ተረባርበው የተፈጠረውን ሁኔታ በማረጋጋት፣ የውጭውን ዓለም በጉዳዩ ላይ መረጃ በመስጠት ማገዝ እና የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በተሳለጠ መንገድ እንዲቀጥል ለማድረግ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቡድኑን አንቀሳቅሶ የድርሻውን እንዲወጣ ለማስተባበር ዘግይቷል የሚል ሀሳብ አንስተዋል።

ቡድኑ በቀጣይ ሁኔታውና ጊዜ በሚፈቅደው የበኩሉን ለመወጣት እንደሚሰራ ቃል የገባ ሲሆን፤ አስፈላጊውን የማስተባበር ሥራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በውጭ ጉዳይ በኩል ሥራውን ለማስተበበር አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ እንደሚሰራ ቃል መግባታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በተጀመረበት ወቅት በታችኞቹ የአባይ ተፋሰስ ሃገራት የተፈጠረውን የተዛባ አመለካከት ለማስተካከል ቢባል ከተለያዩ የህብረተሰብ አካላት የተውጣጣ ቡድን በጎረቤት ሃገራት የሥራ ጉብኝቶችን በማድረግ በመንግሥት ለሚደረገው የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ የበኩሉን ሲያደርግ የቆየ አካል መሆኑ ይታወቃል።

 

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.