Fana: At a Speed of Life!

ከ116 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ116 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
 
ኮሚሽኑ ባሳለፍነው ሳምንት ባደረገው ክትትል ነው 102 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 14 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር የወጪ፣ በድምሩ 116 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የተያዙት፡፡
የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ሞያሌ፣ አቃቂ ቃሊቲ እና ድሬድዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሲሆኑ በቅደም ተከተላቸው 30 ነጥብ 5 ሚሊየን፣ 18ነጥብ 7 ሚሊየን እና 5 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ ችለዋል፡፡
 
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች ፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ ሲሆኑ÷ የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 6 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
 
በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት ፣ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ጫት፣ አደንዛዥ እጾች እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች የሚገኙበት መሆኑን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.