Fana: At a Speed of Life!

ከ3 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ገብቷል – የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአማራ ክልሉ በ2014/15 የመኸር እርሻ አገልግሎት ላይ የሚውል ከ3 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ መግባቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አጀበ ስንሻው ለአማራ ክልል በ2014/15 ዓ.ም የመኸር እርሻ አገልግሎት ላይ የሚውል ሰው ሠራሽ ማዳባሪያ 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል መመደቡን ጠቁመው÷ እስካሁን ድረስም ከ3 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ገብቷል ብለዋል።
ከ2 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል በላይ ያህል የአፈር ማዳበሪያም በክልሉ ከሚገኙ ዩኒየኖች እና ኀብረት ሥራ ማኀበራት መድረሱንም ነው የገለጹት፡፡
ዩኒየኖች እና ኅብረት ሥራ ማኅበራት ላይ ከደረሰው ማዳበሪያ ከ2 ነጥብ 23 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በአርሶ አደሩ እጅ ገብቶ አገልግሎት ላይ መዋሉንም አንስተዋል፡፡
ምርጥ ዘርን በተመለከተም÷ በዚህ ዓመት 219 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር መሰብሰቡን ገልጸው÷ ከተሰበሰበው ውስጥም 197 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ተበጥሮ ለዘር መዘጋጀቱን አመላክተዋል።
በዚህ ዓመትም ከ86 ሺህ ኩንታል በላይ የበቆሎ ምርጥ ዘር በአርሶ አደሩ እጅ መግባቱን እና ጥቅም ላይ መዋሉንም ተናግረዋል።
የክልሉ የምርታማነት መጠን 26 ኩንታል በሄክታር መሆኑን ጠቁመው÷ ይህን ችግር ለመቅረፍ እና ምርታማነትን ለማሳደግ አልሞ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ሁሉም አርሶ አደሮች የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ በመጠቀም ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው የጠቆሙት ምክትል ቢሮ ኃላፊው በየደረጃው ያሉ የግብርና ባለሙያዎችም ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.