Fana: At a Speed of Life!

ከ39 ሺህ በላይ ሃሰተኛ የብር ኖት ወደ ባንክ አካውንቱ ሊያስገባ የሞከረ ተጠርጣሪ እጅ ከፍንጅ ተያዘ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ከ39 ሺህ በላይ ሃሰተኛ የብር ኖት ወደ ባንክ አካውንቱ ሊያስገባ የሞከረ ተጠርጣሪ እጅ ከፍንጅ ተይዞ ምርመራ እየተደረገበት እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር የዋለው ትናንት በክፍለ ከተማው ወረዳ 1 በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ረጲ ቅርንጫፍ ውስጥ ነው፡፡

ግለሰቡ በባለ ሁለት መቶ የብር ኖት 39 ሺህ 800 ሃሰተኛ ብር ይዞ ወደ ባንኩ በመሄድ የገንዘብ ገቢ ማድረጊያ ፎርም ከሞላ በኋላ ገንዘቡን ገቢ ለማድረግ ሲሞክር የባንኩ የሂሳብ ሰራተኞች ተጠራጥረው በሰጡት ጥቆማ ነው በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አባላት እጅ ከፍንጅ ተይዞ ምርመራ እየተደረገበት የሚገኘው፡፡

ሀሰተኛ ገንዘብ በመጠቀም በህገ-ወጥ መልኩ ተጠቃሚ ለመሆን ወንጀል የሚፈፅሙ ጥቂት ግለሰቦች ከግለሰብም አልፎ መንግስትን ለማጭበርበር እስከመሞከር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በህብረተሰቡ መረጃ ሰጪነት እየከሸፈ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል፡፡

ወንጀልን በዘላቂነት ለመከላከል እና ከምንጩ ለማድረቅ ፖሊስ እያከናወነ ያለውን ተግባር በመደገፍ ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ መቅረቡን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.