Fana: At a Speed of Life!

ከ75 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባሳለፍነው ሳምንት 75 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢና የወጭ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ ባሳለፍነው ሳምንት ባደረገው ክትትል ነው 41 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 33 ነጥብ 7 በላይ ሚሊየን ብር የሚያወጡ የወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች  የተያዙት፡፡

የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ድሬድዋ፣ ሀዋሳ፣ ኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሲሆኑ÷ በቅደም ተከተላቸው 12 ነጥብ 9 ሚሊየን፣ 10 ነጥብ 3 ሚሊዮን እና 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ መቻላቸው ተገልጿል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ ሲሆኑ÷ የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ አምስት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተመላክቷል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሃኒት ፣ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ጫት፣ አደንዛዥ እጾች እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል ተብሏል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የህግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች ፣ የክልልና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለመላው ህዝብ ምስጋና ማቅረቡን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.