Fana: At a Speed of Life!

ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች  ማሳደግ እንደምትፈልግ ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ገለጸች።
በኩባ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ከኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቡሩኒ ሮድሪጌዝ ፓሪላ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይታቸው ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(UNIDO) ዋና ዳይሬክተርነት የአፍሪካ ሕብረት ዶክተር አርከበ እቁባይን በእጩነት ማቅረቡን በተመለከተ እና በቀጠናዊና የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ያተኮረ መሆኑ ተመላክቷል።
አምባሳደር ሽብሩ ኢትዮጵያ ከኩባ ጋር ላላት ግንኙነት የላቀ ግምት እንደምትሰጥ እና የሁለቱን ሃገራት ዘርፈ-ብዙ ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በዚህም በጤና፣ በትምህርት እና በተለያዩ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም የሕዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዶክተር አርክበ እቁባይ ለተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትራ ልማት ድርጅት ጄኔራል ዳይሬክተርነት በዕጩነት ማቅረቧንና መጨረሻ ሦስት ዕጩዎች ውስጥ መካተታቸውን በአፍሪካ ህብረት በኩል ሙሉ ድጋፍ የተሰጣቸውን የአፍሪካ ብቸኛ ተወዳዳሪ መሆናቸውን በመጥቀስም፥ ዶክተር አርከበ ካላቸው ብቃት እና ድርጅቱን ለመምራት ካስቀመጡት ሪዕይ አንጻር ቢመረጡ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በማደግ ላይ ላሉ ሃገራት ጠቃሚ መሆኑን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰፋ ያለ ገለፃ አድርገዋል።
አምባሳደሩ አያይዘውም ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ ከግብጽና ሱዳን ጋር ያሉትን ልዩነቶች በውይይትና በድርድር ለመፍታትና ሁሉንም ወገን በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሃዊ ስምምነት እንዲደረስ ቁርጠኛ አቋም እንዳላትም ነው የገለጹት፡፡
ከዚህ አንጻርም ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ መፍትሄ የሚያገኝበት ሁኔታ እንዲፈጠር እየሰራች መሆኑን አብራርተዋል።
በተጨማሪም ስለ ኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ፣ በቅርቡ ስለሚካሄደው 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ እና መንግስት በትግራይ ክልል ስላካሄደው የህግ የበላይነት የማስከበር እርምጃ በተመለከተም ለሚኒስትሩ ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡
የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው ÷ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው መንግስት የሚያካሂደውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሪፎርም እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።
ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተቀራርበው ለመስራት መንግስታቸው ቁርጠኛና ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግስታ ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ያቀረበቻቸውን እጩ ኩባ በአዎንታዊ መልኩ ወስዳ እንደዝምታየው ጠቅሰው÷የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች ማሳደግ እንደምትፈልግም አውስተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይዋን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራሷ ለመፍታት እያከናወነች ያለውን ተግባር ኩባ እንደምትደግፈውና እውቅና እንደምትሰጠው መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.