Fana: At a Speed of Life!

ከቀድሞዋ ሚስቱ ለወለደው ሕፃን ማሳደጊያ ላለመክፈል 1 ሚሊየን የካናዳ ዶላር ያቃጠለው ግለሰብ

አዲስ አበባ፣የካቲት 3፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) ከቀድሞዋ ሚስቱ ለወለደው ሕፃን ማሳደጊያ ላለመክፈል 1 ሚሊየን የካናዳ ዶላር ማቃጠሉን ለፍርድ ቤት ያስታወቀው 55 ዓመቱ ካናዳዊ ነጋዴ ድርጊት እያነጋገረ ነው።

የኦቶዋው ነዋሪው ብሩስ ማኩንቪሌ የተባለው ይኸው ግለሰብ በግምት 750 ሺህ የሚሆን የካናዳ ዶላር ከስድስት የተለያዩ የባንክ ሂሳቦች በ25 ዙር ወጪ ማድረጉን ገልጿል።

ከዚህ በኋላም በሁለት ዙሮች ማለትም በፈንጆቹ መስከረም 23 ቀን 743 ሺህ የካናዳ ዶላር  እና ታህሳስ  15  296 ሺህ  የካናዳ ዶላር ማቃጠሉን ፍርድ ቤት ቀርቦ ለዳኛው ተናግሯል፡፡

ነጋዴው ምንም እንኳን በትዳሩ የፍቹ ሂደት በብስጭት ገንዘቡን ቢያቃጥልም የልጆቹን ፍላጎት ላይ ተጽእኖ  እንዳለው እንደሚያውቅ  ለፍርድ ቤት ዳኛው ገልጿልም ተብሏል፡፡

ግለሰቡ በተለምዶ ይህን ላደርገው የምችለው ነገር አይደለም ሁሌም ቁጥብ እና ጥንቁቅ ነኝ ለዚያ ነው ንግዴ ለ31 ዓመታት የዘለቀው ብሏል፡፡

ገንዘቡን ወጪ ያደረገበት ደረሰኝ እንዳለው የሚጠቁም መረጃ ቢኖረውም በትክክል ስለማቃጠሉ የአይን እማኝም ሆነ በቪድዮ የተቀረጸ ምስል በማስረጃነት አለመቅረቡ ነው የተጠቆመው፡፡

የከፍተኛው ፍርድ  ቤት ዳኛ ኬቪን ፊሊፕስ ማኮንቪል ተከሳሹ ያደረገውን ለማመን  በጣም ከባድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አላምንህም እውነተኛ አንደሆንክ አላስብም ፍርድ ቤቱን ማሾፊያና መሳለቂያ ለማድረግ በመሞከርህ፣ትክክለኛ የፍትህ አስተዳደሩን ሆን ብሎ ለማደናቀፍ በማሰብህ፣ ከምንም በላይ የልጅህን ፍላጎት የሚጎዳ ተግባር በመፈጸምህ የ30 ቀናት እስራትን ወስኜብሀለሁ ብለዋል፡፡

ዳኛው በተጨማሪም ብሩስ ከዚህ ድርጊት እንዲታቀብና ወደ ፊት  ፍርድ ቤት  በሚቀርብበት ጊዜ   እውነቱን ካልተናገረ  ከባድ ቅጣት እንደሚጠብቀው ተናግረዋል፡፡

በሌላም በኩል ባለሀብቱ ንብረቱን እንዳይሸጥ በፍርድ ቤት ቢታዘዝም ለቀድሞው የሂሳብ ባለሙያው አንዳንድ ንብረቶቹን በመሸጥ ላይ መሆኑም ነው የተጠቆመው ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ግለሰቡ ስለገንዘቡ የሚገልጽ የሂሳብ ማረጋገጫ ለፍርድ ቤቱ እንዲያቀርብ ቢጠየቅም ሊያቀርብ አለመቻሉም ነው የተገለጸው፡፡

የገንዘብ አቅሙ ሚስጥር በሆነበት ሁኔታ ፍርድ ቤቱ ለልጁ እና ለባለቤቱ ምን ያህል መክፈል እንዳለበት መወሰን ሳይቻል መቆየቱ የተገለፀ ሲሆን÷በቅርብ በተካሄደው ችሎት ለቀድሞ ባለቤቱ በቀጥታ በየቀኑ 2 ሺህ ዶላር እንዲከፍል መወሰኑም ተመላክቷል፡፡

ምንጭ፡- odditycentral

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.