Fana: At a Speed of Life!

ካናዳ በዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላን ለሞቱ ዜጎቿ ትክክለኛ ምላሽ እንደምትሻ ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ጥር4 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ካናዳ በኢራን ተመቶ በወደቀው የዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላን ለሞቱ ዜጎቿ ትክክለኛ ምላሽ እንደምትሻ ገለጸች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ሃገራቸው ለሞቱ ዜጎቿ “ትክክለኛ ምላሽና ፍትህን ከኢራን ትሻለች” ብለዋል።

ኢራን ባለፈው ቅዳሜ ንብረትነቱ የዩክሬን የሆነውን የመንገደኞች አውሮፕላን ተፈጠረ ባለችው ስህተት መታ መጣሏን ተከትሎ በውስጡ ነበሩ 176 ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል።

ከእነዚህ መካከል 57ቱ ካናዳውያን መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሟቾች በተዘጋጀው የመታሰቢያ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ለሞቱ ካናዳውያን “ፍትህን እንሻለን፤ ትክክለኛ ምላሽም ይሰጠን” ብለዋል።

ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ሊከሰት አይገባም ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የሟች ቤተሰቦችም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የእርሳቸው ድጋፍ እንደማይለያቸው ገልጸውላቸዋል።

ኢራን የዩክሬንን የመንገደኞች አውሮፕላን “በተፈጠረ ስህተት” መታ መጣሏን ዘግይታም ቢሆን ስታምን፥ ይህን ተከትሎም የሃገሬው ዜጎች በመንግስታቸው ላይ ተቃውሞ እያሰሙ ይገኛል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.