Fana: At a Speed of Life!

ኮሚሽነር ጀኔራል እንደሻው ጣሰው እና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ከእስራኤል ምክትል የደህንነት ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2013 (ኤፍ.ቢሲ) ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል እንደሻው ጣሰው እና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ከእስራኤል ምክትል የደህንነት ሚኒስትር ጋዲ ቫርከን ጋር ተወያዩ፡፡
ኮሚሽነሩ ከደህንነት ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ውይይት ስለ ወቅታዊ ሀገራዊ የፀጥታ ጉዳይና ስለፖሊስ ሪፎርም እንዲሁም ልዩ ልዩ የፖሊስ ለፖሊስ ድጋፍና ትብብር ላይ መክረዋል፡፡
እንዲሁም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ከእስራኤል ምክትል የደህንነት ሚኒስትር ጋዲ ቫርከን ጋር የተወያዩ ሲሆን በውይይቱ የሁለቱን ሀገራት ጥንታዊ መሰረት ያለው ግንኙነት በሰፊው ተነስቷል፡፡
ወደ ፊትም ይህን ጥንታዊ ግንኙነት ለማጠናከር በሁለቱም ሀገራት በኩል የባህልና የታሪክ ትስስር ላይ የሚሰራ ኮሚቴ በቅርቡ ተዋቅሮ ግንኙነት ይጀምራል የተባለ ሲሆን ÷ኮሚቴውም በየአመቱ የሚዘጋጅ የልምድ ልውውጥና የግንኙነት መድረክ በመፍጠር መደበኛ የህዝብ ለህዝብ ትብብሩን እንዲያስቀጥል ታስቧል፡፡
በሌላ በኩል በእየሩሳሌም የኢትዮጵያውያን ይዞታ በሆነው የዴር ሱልጣን ገዳም ላይ የሚነሱ ጉዳዮችን በማስተካከል ስፍራው የሁለቱ ሀገራት ጥንታዊ ትስስር ህያው ማሳያ እንደመሆኑ በእስራኤል መንግስት በኩል ተገቢው ጥበቃ እና ልማት እንዲደረግለት ሚኒስትሯ ጠይቀዋል፡፡
ምክትል የደህንነት ሚኒስትሩ ጋዲ ቫርከን በበኩላቸው የኢትዮጵያ እና የእስራኤል ህዝብ በተለየ ሁኔታ የተቆራኘ እና የሚጋራው ታሪክ እና ባህል ለትውልድ መተላለፍ ያለበት መሆኑን አንስተዋል፡፡
ቤተ እስራኤላውያንም በኢትዮጵያ ልዩ ታሪክ አላቸው ያሉት ጋዲ በነበሩበት አካባቢ ያሉ ታሪካዊ ቦታዎች ተጠብቀው እንዲለሙ እና ለታሪክ እንዲሻገሩ ጠይቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ በኢትዮጵያውያን ይዞታ ከሆነው የዴር ሱልጣን ገዳም ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄም በጉዳዩ ላይ ቀደም ብለው ከእየሩሳሌም ከተማ ከንቲባ ጋር በመነጋገር እና ክትትል የሚያደርግ ሰው በመመደብ ችግሩ እንዲፈታ እና ይዞታው ተጠብቆ እንዲለማ እየሰሩ መሆናቸውን መናገራቸውን ከባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.