Fana: At a Speed of Life!

ኮርፖሬሽኑ በ40 ቢሊየን ብር የኮንትራት ውል 50 የግንባታ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ነው

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 11 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮ በጀት ዓመት ከ40 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ በሚጠይቅ የኮንትራት ውል 50 የግንባታ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታውቋል።
 
ኮርፖሬሽኑ በአቃቂ ቃሊቲ የሚገኘውን “የተገጣጣሚ ህንፃ ግንባታ ማምረቻ ማዕከል” ከፌደራል፣ ከክልልና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ለተወጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች አስጎብኝቷል።
 
ጉብኝቱ በኮንስትራክሽን ግብዓት ምርት እና ተገጣጣሚ ህንፃ አካላት ቴክኖሎጂ ረገድ እየተካሄደ የሚገኘውን ውጤታማ ተሞክሮ ለማጋራት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
 
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው ለከተሞች የቤት ግንባታ ልማት አጋዥ የግንባታ እቃዎች አቅርቦት ላይ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
 
የተጎበኘው ማዕከል ለውሃ፣ ለቤት፣ ለትራንስፖርት፣ ለመስኖና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ግንባታ ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ እቃዎችን በማምረት ከውጭ የሚገባውን ምርት ለማስቀረት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
 
ከዚህ ባለፈም በ2014 በጀት ዓመት ከ40 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ የኮንትራት ውል የመስኖ መሰረተ ልማት፣ የመንገድ፣ የቤቶች ልማትና ሌሎች ለሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ጨምሮ 50 የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን ኮርፖሬሽኑ እያካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።
 
በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠሩ የሰላም ችግሮች የመቀዛቀዝ አዝማሚያ ቢታይም ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
 
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሄኖስ ወርቁ ኮርፖሬሽኑ እያካሄደው ያለው የግንባታ ምርት ኢትዮጵያ ሃብቶቿን በአግባቡ በመጠቀም እድገት ማረጋገጥ እንደምትችል ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
 
ኮርፖሬሽኑ የተጣሉ ሃብቶችን መልሶ በማምረት ለመጠቀም የጀመረው ጥረት ከውጭ የሚገቡ የግንባታ ጥሬ እቃዎችን ለመተካት የሚረዳ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.