Fana: At a Speed of Life!

ኮቪድ 19 ጠንካራ የጤና ስርዓት የብሄራዊ ደህንነት ጉዳይ መሆኑን አስተምሮናል- ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኮቪድ 19 ጠንካራ የጤና ስርዓት መኖር የብሄራዊ ደህንነት ጉዳይ መሆኑን አስተምሮናል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ።

70ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጠና ኮሚቴ ጉባዔ በዛሬው እለት በቪዲዮ ኮንፍረንስ ተካሂዷል።

በጉባዔው ላይም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በቪዲዮ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ በመልእክታቸውም ባለፉት 8 ወራት ዓለማችን በኮቪድ 19 ምክንያት ተፈትናለች ብለዋል።

በዓለም ላይ በፍጥነት እየተሰራጨ ያለው የኮሮና ቫይረስ በአጭር ጊዜ ውስጥ በዓለም ዙሪያ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን አጥቅቷል፤ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሀይወትም ቀጥፏል ሲሉም ተናግረዋል።

የኮሮና ቫይረስ ጤናችንን ብቻ ሳይሆን፣ የአኗኗር ዘይቤያችንን፣ ማህበራዊ እሴቶቻችንን እንዲሁም ኢኮኖሚያችንን በክፉኛ ጎድቷል ያሉ ሲሆን፥ ልጆቻችንን ወደ ትምህርት ቤት አንዳንልክ ከልክሎናል፤ ሰዎች አንድ ቦታ ላይ እንዳይሰበሰቡ እንዲሁም የሚያመልኩበትን መንገድን እንዲቀይሩ አስገድዷል ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስን ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መሆኑን ካወጀበት ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ መንግስት የቫይረሱን ስርጭት እና የሚያስከትለውን ጫና ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎችን ስትወስድ መቆየቱንም አንስተዋል።

እርምጃዎቹ ኢትዮጵያን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል እንዲሁም በአፍሪካ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ ታስበው የተወሰዱ ናቸው ብለዋል።

ቫይረሱ በኢትዮጵያ ከመታየቱ በፊት በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን የቁጥጥር ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፤ ቫይረሱ በኢትዮጵያ ከተከሰተ በኋላ ግን “በመደመር” እሳቤ መርህ የጋራ አመራር በመስጠት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዚሁ የመደመር እሳቤ መሰረት ከጃክ ማ ጋር በመሆን በአምስት ዙር የኮሮና ቫይረስ መከላከያ እና መመርመሪያ ቁሳቁሶችን ለአፍሪከ ሀገራት እንዲከፋፈል ማድረጋቸውንም በማንሳት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድም በዚህ ፈታኝ ወቅት የአፍሪካ አለኝታነቱን አረጋግጧል ብለዋል።

አሁንም ቢሆን የአፍሪካ አህጉር በኮቪድ 19 ፈታኝ ወቅት ላይ እንደምትገኝ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ የኮቪድ 19 ጫናን ለመቀነስ ሶስት ወሳኝ ነጥቦችንም አጋርተዋል።

እነዚህም የመጀመሪያው በትብብር የሚደረጉ ጥረቶችን ማጠናከር፣ ሁለተኛው አፍሪካ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የኮቪድ 19 ክትባትንና ህክምናዎችን ማግኘት በሚቻልበት መንገድ ላይ የጋራ አቋም መያዝ ሲሆን፥ ሶስተኛው ደግሞ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የጤና ስርዓትን ማጠናከር ነው ብለዋል።

ኮቪድ 19 ጠንካራ የጤና ስርዓት የብሄራዊ ደህንነት እንዲሁም የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ መሆኑን አስተምሮናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ የአፍሪካ ሀብረትም ይሁን በቀጠናዊ በይነ መንግስታት ላይ የጤና ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባም አስታውቃል።

በዚህ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ድጋፍ በማድረግ እና በተለያዩ መስኮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ነው ላሏቸው የዓለም ጤና ድርጅት እንዲሁም የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰም በጉባዔው ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን፥ በንግግራቸውም ኢትዮጵያ በጥር ወር ላይ ቫይረሱን የመመርመር አቅም እንዳልነበራት ጠቁመዋል።

አሁን ላይ ግን ከዜሮ ተነስታ በቀን እስከ 20 ሸሰዎችን የመርመር አቅም መፍጠር መቻሏንም ነው ዶክተር ሊያ በንግግራቸው ያመላከቱት።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.