Fana: At a Speed of Life!

ወይዘሮ አዳነች አቤቤና አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሾላ ወተት ማቀነባበሪያ ማስፋፊያን መረቁ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሾላ ወተት ማቀነባበሪያ ማስፋፊያን መረቁ፡፡

ሾላ ወተት በ66 ሚሊየን ብር ወደ ግል ከዞረ በኋላ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ 40 ሺህ ሊትር ወተት የሚያመርተውን ማቀነባበሪያ ወደ 90 ሺህ ሊትር ከፍ እንዲል አድርጎታል።

ቀጥሎም በ610 ሚሊየን ብር 41 ሺህ ካሬ ላይ በተደረገ ማስፋፊያ 24 ሰዓት የሚሰራ ሲሆን በማስፋፊያውም የሚያመርተውን ምርት በቀን 320 ሺህ ሊትር ከፍ ማድረግ ችሏል።

ፋብሪካው አሁን ላይ 400 ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን፥ ከዚህ በፊት ወተት ይሰበስብባቸው ከነበሩት በተጨማሪ 14 የወተት ማሰባሰቢያ ጣቢያዎችን አቋቁሟል።

አዲስ የወተት ማሸጊያ የፕላስቲክ ጠርሙስም አስተዋውቋል።

የሚድሮክ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ የወተት ማቀነባበሪያው ሙሉ ለሙሉ ከሰው እጅ ንክኪ ነጻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም በከተማዋ የሚታየው የኑሮ ውድነት አንዱ ምክንያት የአቅርቦት ማነስ መሆኑን በመግለጽ በተለይ የወተት እጥረት ህጻናትን በቀጥታ የሚጎዳ በመሆኑ ሚድሮክ ግሩፕ ለሰራው ስራ ምስጋና አቅርበዋል።

ሌሎች በለሀብቶችም በዚህ መልኩ የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ስራዎችን ቢሰሩ ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል  ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሺመልስ አብዲሳ በበኩላቸው ሀገር በቀል አምራች በመሆን ቀዳሚ የሆነው የሚድሮክ ግሩፕ በኦሮሚያ ክልልም በተለያዩ ዘርፎች በመሰማራት ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ምንም እንኳን በግብርናው ዘርፍ ራሷን ችላ ለውጭ ሀገራትም መላክ የምትችልበት አቅም ቢኖራትም እስካሁን ግን አብዛኛውን የግብርና ምርት ከውጭ እያስገባች እንደምትገኝ በመጥቀስም አሁን እየተደረጉ ባሉ የለውጥ ስራዎች አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እየሆነ ምርት እንዲጨምር እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዘመን በየነ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.