Fana: At a Speed of Life!

ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ላሉ ዜጎች የኢንቨስትመንት አማራጮች መመቻቸታቸውን የአፋር ክልል እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኢድ እስከ ኢድ አገራዊ ጥሪን ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ለሚገኙ ዜጎች የኢንቨስትመንት አማራጮች እየተመቻቹ መሆኑን የአፋር ክልል እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አስታወቁ፡፡

የአፋር ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኤሻ መሀመድ፥ የበርካታ ተፈጥሮ ሃብቶች ባለቤት የሆነው ክልሉ ለዳያስፖራው ማህበረሰብ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

ከኢድ እስከ ኢድ አገራዊ ጥሪን ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት የሚገቡ ወገኖች በክልሉ በማዕድን፣ እርሻ እና እንስሳት ልማት ዘርፍ መሰማራት እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡

በዳሎል፣ ኤርታሌ እና ሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶችን በኢንቨስትመንት ማልማት ላይ በበቂ ሁኔታ እንዳልተሰራ ጠቁመው፥ ዳያስፖራው በሆቴል፣ ቱሪስት እና በሌሎች መስኮች መሰማራት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር፥ ከዚህ በፊት ገናን ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት በገቡ ዜጎች የተጀመሩ የኢንቨስትመንት ስራዎች በኢድ እስከ ኢድ መርሐ ግብር እንዲነቃቁ ሆነዋል ብለዋል፡፡

ከተማዋ ካላት የኢንዱስትሪ ዞን እና ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች አንጻር ከ20 በላይ ዘርፎች መለየታቸውን ገልጸው፥ ዳያስፖራው በሆቴልና ቱሪዝም፣ ማምረቻ ኢንዱስትሪ እና ሎሎች መስኮች በከተማዋና አካባቢው መሳተፍ እንዲችሉ አማራጮችን የማስተዋወቅ ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል፡፡

ጥሪውን ተከትሎ እየመጡ ለሚገኙና ከዚህ ቀደም የመጡ ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙም ትኩረት መሰጠቱን የስራ ኃላፊዎቹ አብራረተዋል፡፡

በአወል አበራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.