Fana: At a Speed of Life!

ውጤታማነትን ታሳቢ ያደረገ የአመራር አደረጃጀት ለመገንባት በትኩረት እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)የሲዳማ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት በሁሉም መስኮች ውጤታማና ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ መስጠትን ታሳቢ ያደረገ የአመራር አደረጃጀት ለመገንባት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።
አመራሩን ለቀጣይ ተልዕኮ ብቁ ማድረግን ዓላማ ያደረገና የ2014 በጀት ዓመት የዝግጅት ምዕራፍ ማጠቃለያ ክልል አቀፍ መድረክ በሐዋሳ ተጀምሯል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እንዳሉት÷ በተጠናቀቀው በጀት አመት በነበረው ሀገራዊ ምርጫ የብልጽግና ፓርቲ ለህዝቡ የገባውን ቃል በተግባር ለመፈጸምና ለመመለስ በልዩ ትኩረት ይሰራል።
ለዚህም እንዲረዳ ከታችኛው መዋቅር እስከ ክልል ማዕከል ድረስ የተቀናጀ የዕቅድ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በተያዘው በጀት አመት የኑሮ ውድነትን ለማርገብ እንዲሁም ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚሰራ የጠቆሙት ርዕሠ መስተዳድሩ÷ በሁሉም አካባቢዎች ያሉ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም የመስኖ ልማትን ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ምርት የሚደብቁና ተገቢ ያልሆነ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎች መኖራቸውን ጠቁመው÷ የደላሎች ሰንሰለትም ምርት በአግባቡ ለሸማቹ እንዳይደርስ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የክልሉ መንግስት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚሰራው ስራ ጎን ለጎን ምርት በሚደብቁና ሌሎች አላስፈላጊ ተግባራትን በሚፈጽሙ አካላት ላይ ጠንካራ ቁጥጥርና እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።
የሲዳማ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ በበኩላቸው ህዝቡ ከነጉድለቱ ብልጽግናን መምረጡ ፓርቲው የገባውን ቃል በተግባር ይፈጽማል በሚል ተስፋ መሆኑን በመገንዘብ ቃላችን በተግባር ልናረጋግጥለት ይገባል ብለዋል።
ለዚህም እንዲረዳ ከክልሉ እና ከሁሉም መዋቅር ከ500 በላይ የሆኑ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ውይይት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮችን ለመፍታት ብቃት ያለው አመራር የሚሰጥ አደረጃጀትን መፍጠር ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
በአመራር ደረጃ የተሰጣቸውን ዕድል መጠቀም ያልቻሉና ህብረተሰቡን በብቃት ማገልገል ያልቻሉ አመራሮች ለውጡን ማስቀጠል በሚችሉ አመራሮች እንደሚተኩ ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.