Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፉ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ተፅዕኖ ፈጣሪ እንዲሆን የባለ-ብዙ ባለድርሻ አካላት አማካሪ ቡድን እየሰራ ነው- ወ/ሮ ሁሪያ አሊ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) ዓለም አቀፉ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ተፅዕኖ ፈጣሪ እንዲሆን የባለ-ብዙ ባለድርሻ አካላት አማካሪ ቡድን እየሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሁሪያ አሊ ገለፁ

የባለ-ብዙ ባለድርሻ አካላት አማካሪ ቡድን የተለያዩ ባለድርሻዎች የተሳተፉበት ስብሰባውን በጄኔቭ እያካሄደ ነው።

በስብሰባው እየተሳተፉ የሚገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሁሪያ አሊ በቀጣይ አመት በኢትዮጵያ የሚካሄደው ዓለም አቀፉ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ተፅዕኖ ፈጣሪ እንዲሆን የባለ-ብዙ ባለድርሻ አካላት አማካሪ ቡድን እያከናወናቸው ላለው ተግባራት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

መድረኩ ከተለመዱ ተሳታፊዎች በተጨማሪ ከአፍሪካ የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪል ማህበረሰብ እና ወጣቶችን በማካተት  አዳዲስ ተሳታፊዎችን የሚስብ እንዲሆን እናደርጋለን ብለዋል።

ጉባኤው የበይነ መረብ ግንኙነት ተደራሽነት እጥረት፣ አንገብጋቢ የበይነመረብ መሰረተ ልማት፣ የዲጂታል ኢኮኖሚን ማፈጠን፣ የዘመኑ የበይነ መረብ ቁሶች እና የሰው ሰራሽ አስተውሎ ላይ እንደሚያተኩር ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም በበይነ መረብ መንታፊዎችና ወንጀለኞች የሚፈፀሙ የማጭበርበር ወንጀሎች እና የሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ 17ኛውን የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤን አስተናጋጅነት ከፖላንድ ተረክባ ዝግጅት እያደረገች እንደምትገኝም አመላክተዋል።

የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ከኢንተርኔት ጋር ተያይዞ ያሉ ዕድሎችን እንዲሁም ፈተናዎችና ተግዳሮቶችን በተመለከተ የሚነሱ ሀሳቦች የሚንሸራሸሩበትና የጋራ ግንዛቤ የሚፈጠርበት መድረክ መሆኑን ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.