Fana: At a Speed of Life!

ዓመታዊ የተሽከርካሪ ፈቃድ ማደሻ /ቦሎ/ ክፍያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ሊፈፀም ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓመታዊ የተሽከርካሪ ፈቃድ ማደሻ ክፍያ ለመሰብሰብ ከመንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን አስታወቀ፡፡

ስምምነቱን የባንኩ የማዕከላዊ ሪጂን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኪዳኔ መንገሻ እና የመንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ራሺድ መሃመድ ፈርመዋል፡፡

በዚሁ ወቅት አቶ ኪዳኔ መንገሻ ስምምነቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ የተሽከርካሪ ባለቤቶችን የዘመናዊ ክፍያ አሠራር ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ነው የገለጹት፡፡

ደንበኞች የክፍያ አገልግሎቱን በባንኩ ቅርንጫፎች፣ በፖስታ ቤት በሚገኙ የፖስ (POS) ማሽኖች እንዲሁም በኢንተርኔት የባንክ አገልግሎት በኩል በፍጥነት ያለእንግልት ማግኘት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡

አቶ ኪዳኔ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 53 በመቶ የሚሆነውን አገልግሎቱን በዲጂታል ስርዓት አማካኝትት በመፈፀም ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ይህም የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን በማስቀረት ህብረተሰቡን የዘመናዊ ክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚ የማድረግ ጥረት አካል ነው ብለዋል፡፡

አቶ ራሺድ መሃመድ በበኩላቸው በዓመታዊ የተሸከርካሪ ፈቃድ ማደሻ ክፍያ ከ3 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚሰበሰብ ገልፀዋል፡፡

የክፍያ አገልግሎቱ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል መደረጉ ደንበኞችንም ጽህፈት ቤቱንም የተቀላጠፈ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ  ገልፀዋል፡፡

በተለይ ከዚህ በፊት ወደ መንገድ ፈንድ መግባት ያለበትን ገንዘብ ሀሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ይፈፀም የነበረውን ማጭበርበር ያስቀራል፣ የጽህፈት ቤቱን የክፍያ መሰብሰብ አቅም ያሳድጋልም ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሃና አራያሥላሴ በበኩላቸው በአዲሱ የክፍያ ስርዓት በባንኩ በቅርንጫፎች፣ ከፖስታ ቤት ቅርንጫፍ ጋር በተገናኘ የፖስ ማሽን እንዲሁም በኢንተርኔት ባንኪንግ አሠራር ክፍያቸውን የፈጸሙ ደንበኞች የሚያገኙትን የክፍያ ደረሰኝ እና የተሽከርካሪ ሊብሬያቸውን ለፖስታ ቤት በማቅረብ የክፍያ ማረጋገጫ ካገኙ በኋላ ለትራንስፖርት ባለሥልጣን በማሳየት ዓመታዊ ቦሎ መውሰድ እንደሚችሉ ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ባንኩ ከዚህ በፊት ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽህፈት ቤት፣ ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ እና ከሌሎች የመንግሥት እና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በመተባበር የተለያዩ ክፍያዎች በባንኩ አገልግሎቶች እገዛ የሚፈጸሙበትን አሠራር ማመቻቸቱ ይታወቃል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.