Fana: At a Speed of Life!

ዛሬ ሁላችንም ላሊበላ ተገኝተን በዓሉን እንድናከብር መተኪያ የሌላት ሕይወታቸውን ለገበሩ ኢትዮጵያውያን ምስጋና ይገባቸዋል-ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 29፣ 2014 ( ኤፍ ቢ ሲ) ”ዛሬ ሁላችንም ላሊበላ ተገኝተን በዓሉን እንድናከብር መተኪያ የሌላት ሕይወታቸውን ለገበሩ ኢትዮጵያያውያን ምስጋና ይገባቸዋል” ሲሉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

የዘንድሮውን የገና በዓል ከእናንተ ጋር ስናከብርም አይዟችሁ አብረናችሁ ነን ለማለት ነውም ብለዋል።

የገና በዓል “ገናን በላሊበላ” በሚል መሪ ሐሳብ ከውጭና ከአገር ቤት በርካታ ታዳሚዎች በተገኙበት በአገር አቀፍ ደረጃ በላሊበላ ከተማ ተከብሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ ”ዛሬ ሁላችንም ላሊበላ ተገኝተን በዓሉን እንድናከብር መተኪያ የሌላት ሕይወታቸውን ገብረው ሰውተው አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው ለዚህ ክብር ላበቁን የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ክልል የጸጥታ ሃይሎች፣ለክልሉ ሕዝብና ለመላው ኢትዮጵያውያን ምስጋናዬን ላቀርብ እወዳለሁ።” ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን የሚያምርብን ከሁሉም ማዕዘናት ተሰባስበን በዓላትን በጋራ ስናከብር ነው ብለዋል።

በአብሮነት ሆነን ገናን በላሊበላ፣ ጥምቀትን በጎንደር፣ መውሊድና አረፋን በአልነጃሽ፣ ፅዮን ማርያምን በአክሱም፣ ኢሬቻን በቢሾፍቱ፣ ጨንበላላን በሀዋሳ እንዲሁም በሌሎች የአገራችን አካባቢዎች በማለት ዘርዝረዋል።

የአብሮነታችን መገለጫ ይህ ሆኖ እያለ በኢትዮጵያ ምድር መሆን የሌለበት፣ መከሰት የሌለበት፣ ወደር የሌለው ጠላትነት፣ አውዳሚነትና የጭካኔ ተግባር በአሸባሪው ህወሓት መፈፀሙን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ ወረራዎችን በመመከት ሉዓላዊነቷን በማስጠበቅ ቅርሶቿንም በጥንቃቄ ይዛ ቆይታለች ብለዋል ፕሬዚዳንቷ።

የአሁኑ ወራሪ ግን ከውጭ የመጣ ሳይሆን የጥፋት ተልዕኮ የያዘ የውስጥ ጠላት ነው ሲሉ የአሸባሪውን ህወሓት አውዳሚነትና የጭካኔ ተግባር ኮንነዋል።

የላሊበላ ከተማም በዚሁ አሸባሪ ቡድን በወረራ ቆይታ በርካታ ወገኖች ተፈናቅለዋል፤ ተጎሳቁለዋል፤ ተደፍረዋል፤ ውድመትና ዘረፋም ተፈፅሟል ብለዋል።

በመሆኑም በአሸባሪው ህወሓት ወደር የሌለው አውዳሚነትና ጠላትነት መታየቱን ጠቅሰው፤ ዳግም እንዳይከሰት ሁላችንም ለአገራችን ሰላምና አብሮነት በጋራ ልንቆም ይገባል ነው ያሉት።

ፕሬዚዳንቷ በመልእክታቸው “የተፈፀመው ሁሉ በእጅጉ ጎድቶናልና በቶሎ ማገገም ይኖርብናል፤ ለዚህ ደግሞ የወደመውን ሁሉ ተባብረን መገንባት አለብን” ብለዋል።

የዛሬውን የገና በዓል ከእናንተ ጋር ስናከብርም አይዟችሁ አብረናችሁ ነን ለማለት እንደሆነም መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያንም በፈረንሳይ መንግስት በተገኘ ድጋፍ እድሳት እንደሚደረግለት አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.