Fana: At a Speed of Life!

ዜጎች በፈለጉት አካባቢ ሀብትና ንብረት አፍርቶ የመኖር መብታቸው እንዲከበር የጋራ ሥራ ያስፈልጋል- የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአግላይነት አመለካከት ለሰላም መደፍረስ አንዱ ምክንያት በመሆኑ ዜጎች በሀገራቸው ውስጥ በፈለጉት አካባቢ ሀብትና ንብረት አፍርቶ የመኖር መብታቸው እንዲረጋገጥ ለማድረግ በጋራ መስራት እንደሚገባ የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ገለጸ፡፡
በክልሉ በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይና የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ጁል ናንጋል፥ በየደረጃው የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በግለሰብም ሆነ በተቋም ደረጃ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የሕዝብ ቅሬታ ከሚታይባቸው ተቋማት መካከል የንግዱ ዘርፍ አንዱ መሆኑን ጠቁመው፥ የንግዱ ማህበረሰብ ሰላማዊ የግብይት ስርዓት በመዘርጋት የሕዝብ ቅሬታዎች እንዳይነሱ ማድረግ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ፥ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን እና በስራ ሂደት ላይ የሚገኙ እንዳሉም ገልጸው÷ ከእነዚህ የልማት ሥራዎች ሕዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻለው ዜጎች ለሰላም ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን ሲችሉ ነው ብለዋል፡፡
የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ሰላም በአስተማማኝ መሠረት ላይ ለማኖር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም ማስገንዘባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በአካቢያቸውና በስራ ቦታቸው ሰላም እንዲሰፍን የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ጠቁመው÷ መንግስትም በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭት የሚያስነሱ አካላትን አድኖ በመያዝ ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.