Fana: At a Speed of Life!

ዜጎች የምርጫ ካርድ ወስደው ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ሊጠቀሙ ይገባል- ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ስድስተኛውን ብሔራዊ ምርጫ  አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ በግንቦት 2013 የሚካሄድ ሲሆን፣ ጥቂት ሳምንታት ብቻ ቀርተውታል።

በመግለጫው ይህ በጉጉት የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ምርጫ በሀገራችን የሚካሄደው የመጀሪያው ነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫ ይሆናል ተብሎ ይታመናል ብሏል።

ከ2010 ዓ.ም. አንስቶ በማስተዳደር ላይ የሚገኘው አመራር የፖለቲካውን ምኅዳር ለማስፋት እና ዴሞከራሲያዊእና እውቀት ተኮር የሆነ ምቹ ከባቢ እንዲኖር ለማስቻል በቁርጠኝነት የዴሞከራሲያዊነት ጎዳናን ተያይዟልም ነው ያለው።

ይህ ግብ ያለ ምንም ተግዳሮት እውን የሚሆን አይደለም ያለው ፅህፈት ቤቱ፥ ይሁን እንጂ የፌደራል መንግሥት ዴሞክራሲያዊነትን ይዞ ለመጓዝ ያለውን ጽኑ ፍላጎት ሳያወላውል መቀጠሉን አውስቷል።

የቀደመው አስተዳደር ዴሞክራሲያዊ አገዛዝን ለመገንባት ካለመቻሉ የተነሳ፣ ኢትዮጵያ ጠንካራ እና ጤናማ ዴሞከራሲያዊ ባህል እና ልምምድ ይኖራት ዘንድ፣ በአሁኑ ወቅት አስፈላጊዎቹን ተቋማት እና አስተሳሰብ የመገንባት ሁለትዮሽ ፈተናን ተጋፍጣለችም ብሏል በመግለጫው።

ኢትዮጵያውያንም ሀገራቸው ለታሪኳ እና ለኩሩ ሕዝቧ መሻት በሚመጥን መልኩ፣ እንዲሁም ያላትን የተትረፈረፈ የዕድገት አቅም ባማከለ ሁኔታ፣ ሀገራቸውን ወደ አዲስ የአስተዳደር እና የብልጽግና ዘመን የማሸጋግር ዕድል እንደቀረበላቸው አውስቷል።

እስካሁን ድረስ፣ የፌደራል መንግሥት የመጀመሪያውን ነጻ፣ ፍትሐዊ እና ሰላማዊ ምርጫ ለማከናወን ያለው ቁርጠኝነት፣ ይህንን ግብ ለማሳካት በሚያካሂደው ያልተቋረጠ ዝግጅት አማካኝነት የተመሰከረ መሆኑንም ገልጿል።

ሰላማዊ እና ሕጋዊ ምርጫ እንዲካሄድ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ከብሔራዊ መረጃና የደህንነት አገልግሎት፣ ከመከላከያ ሚኒስቴር እና ከክልል አመራሮች ተውጣጥቶ ሀገር አቀፍ የምርጫ ደህንነት ኮሚቴ በመንግሥት መዋቀሩንም ጠቅሷል።

ዜጎች በነጻነት የመምረጥ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ይጠቀሙ ዘንድ የመንግሥት ሚና ምን መሆን እንዳለበት ውይይቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውንም አስታውሷል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ግጭት ሊከሰት እንደሚችል ምልክት የሚታይባቸውን አካባቢዎች ለመለየት ኮሚቴው ልዩ እርምጃዎች መውሰዱንም ፅህፈት ቤቱ አንስቷል።

ከምርጫ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎችን ለማስተናገድም፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የምርጫ አቤቱታ የሚያደምጥ ችሎት ማቋቋሙን በመጥቀስም፥ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመላው ሀገሪቱ የምረጡኝ ቅስቀሳ በስፋት እያካሄዱ መሆናቸውንም ነው የገለጸው።

መራጮች በእውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ማድረግ እንዲችሉም ብሔራዊ ጠቀሜታቸው የተመሰከረላቸው ገለልተኛ የመገናኛ ብዙሀን ተቋማት እና የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት የሚሳተፉበት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዴሞክራሲያዊነት እንዲስፋፋ ባላቸው የላቀ ፍላጎት እና ቁርጠኝነት ከክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመራሮች ጋር የሚያደርጉትን ስብሰባ በመቀጠል፣ በምርጫ ቅድመ-ዝግጅት ሂደቱ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን እና ተግዳሮቶችን ለይቶ የመፍታት ጥረታቸውን ቀጥለዋልም ነው ያለው።

በዚህም መሠረት፣ የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም. እና ሚያዝያ 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበይነ መረብ በታገዘ ስብሰባ አማካኝነት፣ በየክልሉ የጸጥታና ደህንነት ጉዳዮችን አፈጻጸም እና የምርጫ ጣቢያዎችን የዝግጅት ሁኔታ መከታተላቸውን ጠቅሷል።

ምርጫው ሊካሄድ ጥቂት ሳምንታት የቀሩት እንደ መሆኑ፣ ዜጎች በቀሪው ጊዜ በመጠቀም የምርጫ ካርድ ወስደው ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙና በምርጫው አጠቃላይ ሂደት ገንቢ ተሳትፎ በማድረግ ነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫ ይካሄድ ዘንድ የጋራ ጥረት እንዲያደርጉ መበረታታት እንዳለበትም አስገንዝቧል።

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.