Fana: At a Speed of Life!

የሀይማኖት ተቋማት በሞጣ በእምነት ተቋማት ላይ የደረሱትን ጥቃቶች አወገዙ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በሞጣ በእምነት ተቋማት ላይ የደረሱ ጥቃቶችን አወገዙ።

በአማራ ክልል በሞጣ ከተማ ቤተክርስቲያንና መስጊዶች መቃጠላቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ባወጡት መግለጫ ነው ድርጊቱን ያወገዙት።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባወጣችው መግለጫ፥ በደረሰው ወቅታዊ እና ያልታሰበ ጉዳት በሀዘን ላይ  ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንና ምዕመናት፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት እና የመጅሊስ አባላት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በሙሉ የተሰማትን ሀዘን ገልፃለች።

የተፈጸመው ድርጊት ለሀገሪቱን ሰላም እና እድገት የማይጠቅም እንዲሁም ለዘመናት የቆየ አብሮ የመኖር ዕሴቶችን የሚንድ በመሆኑ መላው ህዝብ ይህን ተረድቶ በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ ጉዳዩ እስከሚጣራ በትእግስት እንዲጠባበቅ አሳስባለች::

የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት አስፈላጊው ክትትል እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርባለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከሚመለከተው የመንግስት፣ የሕግ እና የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ጉዳዩን በማጣራት ይፋ እንደሚደረግም አስታውቃለች።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፥ በትናንትናው እለት በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ ያልተረጋገጠ ወሬ በመሰራጨቱ ምክንያት መስጊዶች ላይ እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።

ይህንን ተከትሎም የደረሰውን ጉዳት የመንግስት አካላት፣ የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያወግዙት ምክር ቤቱ በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል።

ለደረሰው ጥቃትና ውድመትም አጥፊዎች በህግ ጥላ ስር ውለው ድርጊቱ ተጣርቶ ለፍርድ እንዲቀርቡም ምክር ቤቱ ጠይቋል።

የአማራ ክልል መንግስት በክልሉ የተለያዩ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በሚገኙ የሀይማኖት ተቋማት እና የእምነቱ ተከታዮች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመከላከል መንግስት ከሀይማኖት ገለልተኛ በሆነ አግባብ በህግ መንግስቱ መሰረት እንዲሰራም ጥሪ አቅርቧል።

ምክር ቤተ፥ ህዝበ ሙስሊሙ አንድነቱን ጠብቆና ተረጋግቶ የሀይማኖቱ መሪ ድርጅት ከሆነው ከመጅሊስ በሚሰጠው አቅጣጫ መሰረት በጋራ እንዲሰራም መልእክት አስተላልፏል።

ህዝበ ሙስሊሙ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በማውገዝ በሀገሪቱ በሚገኙ ሁሉም መስጊዶች በየእለቱ ቁነትና ዱአ እንዲሁም በጾምየመጣውን መከራ ፈጣሪ እንዲመልሰው ዱአ እንዲያደርጉም ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

መጅሊሱ ጉዳዩን የሚያጣራ የልኡካን ቡድን ወደ ቦታው የሚልክ መሆኑንና ውጤቱንም በዝርዝር መረጃ ለህዝቡ ይፋ እንደሚያደርግ ነው ያስታወቀው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.