Fana: At a Speed of Life!

የሃይማኖት መሪዎች ነገ የሚጀመረውን ጾመ ፍልሰታ ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣2012 ( አኤፍ.ቢ.ሲ) የሃይማኖት መሪዎች ነሀሴ አንድ ተጀምሮ ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት የሚቆየውን ጾመ ፍልሰታ ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ÷ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ እኩሌታ ለሚጾመው ጾመ ፍልሰታ እንኳን አደራሳችሁ ብለዋል።

ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱቨም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ÷ የዘንድሮው ጾመ ማርያም የሚጾመው ኢትዮጵያና ህዝቦቿ በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋ ተከበው ባሉበት ወቅት ነው ብለዋል።

ብጹዕነታቸው ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ከእነዚህ አደጋዎች ለመውጣት እግዚአብሔርን መፍራትና ንሥሐ መግባት እንደሚያስፈልጋቸው አመልክተዋል።

“እግዚአብሔርን መፍራት ማለት በምንሰራው ሥራ፤ በምንናገረው ቃል፤ በምናስበው ሀሳብና ምኞት ሁሉ እግዚአብሔር ያውቅብናል፣ ይፈርድብናል፣ ያየናል የሚል አስተሳሰብ በውስጣችን አድሮ ከክፉ ድርጊት መቆጠብ ነው” ማለት መሆኑን አስረድተዋል።

ብጹዕነታቸው አያይዘውም “ኢትዮጵያ የዚህ ትውልድ ብቻ ሳትሆን ያለፈውም የወደፊቱም ጭምር ናት” ያሉት ብፁዕነታቸው ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይቶ መፍታትና ለመጭው ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ አለብን ብለዋል።

በመሆኑም ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ቆመናል የሚሉ ሁሉ ልዩነቶችን በውይይት ፈተው የአገሪቱን ሰላም፣ አንድነትና ልማት እንዲያስቀጥሉ ተማፅነዋል።

ሕዝበ ክርስቲያኑ የድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታን ኮቪድ-19ን በመከላከል፣ የተቸገሩትን በመርዳት እንዲያሳልፍ አቡነ ማትያስ ጥሪ አቅርበዋል።

ሕዝቡ ከይቅርታና እርቅ፤ ከሰላምና አንድነት የተሻለ የችግሮች ማሸነፊያም ሆነ ማስወገጃ እንደሌለው መገንዘብ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም ፆመ ፍልሰታ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣውን የጥንቃቄ መመሪያ በማክበር እንዲከናወን አሳስባለች።

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ለ2012 ዓ.ም የፍልሰታ ፆም እንኳን አደረሳችሁ በማለት ለካቶሊክ እምነት ተከታዮች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ምዕመኑ መንግሥትና ቤተክርስቲያኗ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል ያስተላለፉትን የጥንቃቄ መመሪያዎች በማክበር ፆምና ፀሎታቸውን እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ካቶሊካውያን በያሉበት ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር በሰላም ፣በመከባበርና እርስ በእርስ በመዋደድ የሃይማኖት ፣የዘር የፆታ ልዩነት ሳያደርጉ በፍፁም ትህትና ድሆችን እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል።

አገሪቱ የገጠማትን የኮቪድ -19 ወረርሽኝን በመከላከልና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተጀመረውን ተሳትፎ በማጠናከር ለመጭው ትውልድ ስነ ምህዳሯ የዳበረ ሰላማዊና የበለጸገች ኢትዮጵያን የመገንባት ተግባራችንን እንቀጥል ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነእየሱስ ምዕመኑ በያለበት አገር ሆኖ ስለ ሰላም፣ስለ ህዝቦች አንድነትና ስለ ኮቪድ መወገድ እንዲፀልይ ጥሪ አቅርበዋል።

ያለአግባብ ሀብት በመሰብሰብ መበልፀግ በኃይል ስልጣን ለመያዝ በማሰብ ብጥብጥ እና ቀውስን ማንገስ በአምላክ ፊት ኃጢዓት መሆኑን ተናግረዋል።

ብፁዕ ካርዲናል አያይዘውም በፖለቲካ መሳተፍ የሚፈልጉ ተፎካካሪዎች የበለፀገች እና የተረጋጋች አገርን መምራት የሚችሉት በሕዝብ ልብ በመንገስ እንጂ፤ ኃይልን፣ ሁከትንና በደልን መሳሪያ በማድረግ መሆን እንደሌለበት ገልጸዋል።

በቅርቡ በተከሰተው ሁከት የሞቱ ወገኖችን በማሰብ ፣ያዘኑትን በማፅናናት የወደመውን ንብረት በጋራ ድጋፍ መልሶ በማቋቋም ፣ዘረኝነትንና ጥላቻን በኢትዮጵያዊ አብሮነት ወደ ፍቅር በመመለስ ፆምን ማሰብ ይገባል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.