Fana: At a Speed of Life!

የሃይማኖት አባቶች ከጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ጋር እየመከሩ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሃይማኖት አባቶች ከጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ጋር እየመከሩ ነው።

በሃይማኖት አባቶች ፀሎት በተጀመረው ውይይት መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ፥ የምክክር መድረኩ በሃይማኖት ሽፋን ለዘመናት ተከባብረው፣ ተዋደውና ተዛምደው የኖሩ የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን ለመለያየት የሚሰሩ አካላትን አውግዘዋል።

የሕዝቦችን አንድነት ለማጠናከር አሉ የተባሉ ክፍተቶችን በመሙላት፣ የተበደሉትን በመካስና የሕዝቦችን ግንኙነትና አብሮ የመኖር እሴት መገንባት ይገባል ብለዋል፡፡

ስንከባበር እና አንድነታችን ስናጠነክር የጠላት መጠቀሚያ አንሆንም፤ አለምም ያከብረናል ያሉት ጠቅላይ ጸሐፊው ለፓለቲካ ትርፍ ሃይማኖትን መጠቀሚያ የሚያደርጉ አካላትን ቦታ መስጠት እንደማይገባም አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፥ በጎንደር ከተማ በተፈጠረው ችግር የሃይማኖት ተቋማትን እንደማይወክል ገልጸው፥ የተጎዱ ሰዎችን ለማፅናናትና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት አለባቸውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የልዑካን ቡድን አባላት በከተማዋ ሰሞኑን ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎችንና ወገኖችን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እድሪስ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀኃፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ እንዲሁም የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ፃዲቁ አብዱ ፣ የክልል የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ የጎንደር ከተማ የክርስትናና እስልምና ሃይማኖት አባቶችና ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በመድረኩ ተገኝተዋል።

በምናለ አየነው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.