Fana: At a Speed of Life!

የሃገር ሽማግሌዎች የሕወኃት ቡድን ከጅምሩ ልዩነቶች በሰላም እንዲፈቱ ምንም አይነት ፍላጎት አልነበረውም

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሃገር ሽማግሌዎች በሕወኃት ውስጥ ያለው ቡድን ልዩነቶች በውይይትና በሰላም እንዲፈቱ ፍላጎት አልነበረውም አሉ፡፡

የሃገር ሽማግሌዎቹ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ወደ ትግራይ ለሽምግልና ተጉዘው የነበሩ መሆናቸው ይታወሳል፡፡

በሱማሌ ክልል የጎሳ መሪ የሆኑት ጋራድ ኩልሚዬ ሕወኃት ኢትዮጵያን በመራበት ዘመን ሁሉ ሕገ መንግስቱን አክብሮ አያውቅም ነው ያሉት።

እርሳቸው በቅርበት የሚያውቁትን የሱማሌ ክልልን እንደምሳሌ ሲጠቅሱ ክልሉ በሞግዚት አስተዳደር ሲመራ ነበር ብለዋል።

የአገሪቷን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ እሴቶች በሙሉ የናደው የህወሃት ቡድን በሕግ ተመራ ሲባል ወደ ጥፋት መሄዱንም ገልጸዋል።

በወቅቱ ከሄድንበት ሽምግልና መታዘብ የተቻለው ሕወኃት ጸረ ሰላምና ለትግራይ ሕዝብም የማይበጅ መሆኑን ነው።

የአማራ ክልል የሽምግልና ስርዓት ማህበር ፕሬዚዳንት ሊቀ ሕሩያን በላይ መኮንን ሌላው በወቅቱ ለሽምግልና ወደ ሰፍራው ከተጓዙት መካከል ናቸው።

በወቅቱ ፓትሪያርኩን ጨምሮ ትላልቅ የኃይማኖት አባቶች፣ ኡጋሶች፣ አሚሮችና አባገዳዎችን እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦችን ያከተተ ቡድን ወደ ስፍራው ለሽምግልና ተጉዞ እንደነበር አስታወሰዋል።

አላማውም በሕወሓትና በማዕከላዊ መንግስቱ መካከል እየተካረረ የመጣውን ልዩነት ለማጥበብና በሽምግልና መቀራረብን ለመፍጠር እንደነበርም ይገልጻሉ።

ሆኖም በወቅቱ ወደ መቀሌ የተጓዙትን የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ህወሃት አክብሮት በመንሳት መልካም አቀባበል እንዳላደረገላቸው አስታውሰዋል።

መቀሌ ሲደርሱ ከፍትሻ ጀምሮ ብዙ እንግልቶችን አልፈው ሽማግሌዎቹ በስብሰባ አዳራሽ ቢታደሙም የህወሃት ቡድን ለሽምግልና ፍላጎት አለማሳየቱን አረጋግጠዋል።

”አሁን ጊዜው አልፏል፤ ከረፈደ ነው የመጣችሁት” በማለት ለሃይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎች ክብር በማሳጣት እንደመለሷቸው ሊቀ ሕሩያን ማስታወሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በወቅቱ ወደ መቀሌ ለእርቅ የተጓዙት የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ሰዎች 60 እንደነበሩ ይታወሳል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.