Fana: At a Speed of Life!

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባውን አካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 9 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 5ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባውን አካሄደ።

በስብሰባው ላይ ባለፈው መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባደረጉት ንግግር ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ኢኮኖሚውበዋና ዋና ዘርፎች ዕድገት ማስመዝገቡን አንስተው ተስፋ ሰጭ የሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለምክር ቤቱ አብራርተዋል፡፡

ከመከላከል እርምጃዎች በተጨማሪ የዕዳ ስረዛ መካሄዱን በማንሳትም የተፈለገውን ያህል ባይሆንም ለቡድን 20 ሃገራት የቀረበው ጥያቄ ተመልሷል ነው ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱ ዓመታዊ ጥቅል ምርት ባለፈው ዓመት ከነበረበት 2 ነጥብ 7 ትሪሊየን ወደ 3 ነጥብ 375 ትሪሊየን ብር መድረሱን ገልጸዋል፡፡

ግብርናው ባለፈው ዓመት በ4 ነጥብ 3 በመቶ፣ ኢንዱስትሪው 9 በመቶ፣ አገልግሎት 5 ነጥብ 3 በመቶ እንዲሁም የጤናና ማህበራዊ ዘርፉ 10 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ማስመዝገባቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

እንዲሁም ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ዕድገት ያስመዘገበው የማዕድን ዘርፉ ሲሆን 91 በመቶ ማደጉን ጠቅሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፋይናንስ አገልግሎት ንዑስ ዘርፉ 10 ነጥብ 2 በመቶ ማስመዝገቡን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም በባንክ ዘርፉ 6 ሺህ 628 ቅርንጫፎች መከፈታቸውን ጠቅሰው18 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበው ይህ የባንክ ዘርፍ ከፍተኛ በሆነ ሁኔታ የስራ አጥነትን ቀንሷልም ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም 38 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ተቀማጭ ወደ ባንክ የገባ ሲሆን 50 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎች ወይም 31 በመቶ ዜጎች ወደ ባንክ ስርዓት መግባታቸውንም አስረድተዋል፡፡

በጥቅሉ ባንኮች አንድ ትሪሊየን ብር መሰብሰባቸውን ተናግረው ባንኮች የሚሰበስቡት ብር እያደገ ሲሄድ የሚያበድሩት ብር እንደሚጨምር ማሳያ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

አብዛኛው 60 በመቶ የተሰበሰበው በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ሲሆን 13 በመቶ በኦሮሚያ፣ 7 በመቶ በአማራ፣ 5 ነጥብ 2 በደቡብ እና ቀሪው በሌሎች ሥፍራዎች ተሰብስበዋል፡፡

ይህ የኢኮኖሚ ዕድገት የተመዘገበው ኮሮናን ተከትሎ ሁሉንም ነገር ባለመዘጋጋቱ ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ዓመት ትራንስፖርት 1 ነጥብ 1 በመቶ፣ ትምህርት 1 ነጥብ 8፣ የህዝብ አገልግሎት 2 ነጥብ 3 እና ቱሪዝም 9 ነጥብ 8 በመቶ የሆነ ዝቅተኛ ዕድገት ማስመዝገባቸውንም ነው የገለጹት፡፡

ከሃገሪቱ የካፒታል በጀት ጋር በተያያዘ ባለፈው ዓመት 115 ቢሊየን ብር እንደነበረ ጠቅሰው ዘንድሮ ወደ 160 ቢሊየን ብር ማደጉንም ነው የተናገሩት፡፡

ይህም ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በላይ ዘንድሮ እንድናስመዘግብ ይረዳናል ሲሉ ነው ለምክር ቤቱ ያስረዱት፡፡

እንዲሁም የግብርና ዘርፉን ማዘመን ኩታ ገጠምን ማስፋት፣ ቴክኖሎጂን ማሳደግ እና መስኖ ማጎልበት ዋነኛ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

የኑሮ ውድነት ከመቀነስ አንጻር በአዲስ አበባ የተከፈተውን ዳቦ ማከፋፊያ አንስተው ከ4 ሺህ በላይ ዜጎች ስራ መያዛቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም መሰል ፋብሪካ በግንባታ ሂደት ላይ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

ፕሮጀክቶችን በተመለከተም አብዛኛዎቹ በችግር የተተበተቡ መሆናቸውን ጠቅሰው ይህንን ለማስተካከል ጊዜ ይጠይቃል ሲሉ ለምክር ቤቱ አብራርተዋል፡፡

የመንግስት የልማት ድርጅቶች እንደ ሜቴክ፣ ስኳር ፋብሪካዎች፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እስከ 600 ቢሊየን ብር ዕዳ እንደነበረባቸውም አስታውሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ተከትሎ በተሰራው ስርዓት የማስያዝ ስራ ከዕዳ ነጻ እንዲሆኑ መደረጉንም ነው ያስረዱት፡፡

ከጣና በለስ ጋር በተያያዘም ፕሮጀክቱ አንድ ሳይሆን 14 ፋብሪካ በውስጡ መያዙን አስታውቀዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሜቴክ በስምንት ዓመታት ውስጥ ማሳካት የቻለው 62 በመቶ እንደነበረም አንስተዋል፡፡

አሁን ላይ 23 ሚሊየን ዶላር ተመድቦለት በስድስት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ገልጸው ኮንትራት የያዘው ኩባንያ ፕሮጀክቱን 85 በመቶ ማድረሱንም ነው ያስታወቁት፡፡

ከሲሚንቶ ምርት ጋር በተያያዘ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ከፋብሪካዎቹ ጋር የጋራ ምክክር ተካሂዷልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

በዚህም ፋብሪካዎቹ የውጭ ምንዛሪ፣ የመለዋወጫ ዕቃ፣ የኃይል አቅርቦት ጥያቄ እና አስተዳደራዊ ጥያቄዎቻቸውን ለመመለስ መሞከሩንም አስረድተዋል፡፡

ይህም ከማምረት አቅማቸው ውስጥ 85 በመቶ እንዲያመርቱ ያስችላቸዋል ያሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሲሚንቶ በኩንታል እስከ 60 ብር መቀነሱን ነው ያነሱት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ምክር ቤት ውስጥ በሰጡት ማብራሪያ ፌደራላዊና አሃዳዊ ስርዓትን የሚያምታቱ አካላት መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው መንግስት አሃዳዊ ሊሆን ነው ብለው የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚያምታቱ አካላት መኖራቸውን ነው ያስረዱት፡፡

በዚህም ፌደራላዊ ማለት ዴሞክራሲ ፤ አሃዳዊ ማለት ኢ-ዴሞክራሲ ነው በማለት እያምታቱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

የተሻለ ዴሞክራሲ ሰፍኖባቸዋል የሚባሉትን የአፍሪካ ሃገራትን እንደምሳሌ በማንሳት ጋና እና ቦትስዋና በአሃዳዊ እንደሚተዳደሩ ጠቅሰዋል፡፡

በጥቅሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚፈቅደውና የሚበጀው የፌደራል ስርዓት መሆኑን ለምክር ቤቱ አስገንዝበዋል፡፡

መንግስታቸው እውነተኛ የሆነውን የፌደራል ስርዓትም እየገነባ ይገኛል ነው ያሉት በማብራሪያቸው፤ ለውጡ ከመጣ ጀምሮም በአንድ ክልል የፌደራል መንግስት ጣልቃ ገብቶ እንደማያውቅም ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.