Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለአፍሪካ አጀንዳ 2063 ስኬት  አስተዋፅኦ እንዳለው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በአልጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ተቀማጭነቱን በአልጀርስ ካደረገው የአፍሪካ ህብረት የኢነርጂ ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት ከአቶ ራሺድ አሊ አብደላህ   ጋር በዛሬው ዕለት  ተወያይተዋል።

አምባሳደር ነብያትበዚሁ ወቅት  ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የፍትሓዊ ተጠቃሚነት ፖሊሲ የምታራምድ መሆኗን ገልጸዋል።

አያይዘውም ግድቡ ለታችኛው ተፋሰስ ሃገራትም የጎላ ጉዳት እንደማያስከትል፣  የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅም ለሌሎች አጎራባች የአፍሪካ ሃገራትም ጥቅሙ የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።

በተጨማሪም አፍሪካን በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር ረገድም የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ከማሳካት አኳያም ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

እንዲሁም በግድቡ ዙሪያ የሚደረገው ድርድር በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት መሆኑ ጉዳዩ አፍሪካዊ መፍትሔ ከማስገኘት አኳያ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ከዋና ዳይሬክተሩ ጋር በተደረገው ዉይይት አምባሳደር ነብያት አንስተዋል ።

ዋና ዳይሬክተሩአቶ ራሺድ አሊ አብደላህ   በበኩላችው÷ የአፍርካ ህብረት አባል ሃገራት ያላቸውን የኢነርጂ ሀብቶች በተቀናጀ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለአባል ሃገራቱ ለፖሊሲ ግብአቶች ሊውሉ የሚችሉ የተለያዩ ዳታዎችና ስታትስቲክስ በማዘጋጀት የማቅረብ ሥራዎች እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

አያይዘውም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የአፍሪካን የኢነርጂ ፍላጎት ከሟሟላት አኳያ እና  የአፍሪካ ሀገራት በኢነርጂ ከማስተሳሰር   እንዲሁም የታዳሽ የኢነርጂ ምንጭ እንደመሆኑ ለቀጣይ የአፍሪካ የልማት እንቅስቃሴዎች እጅግ የጎላ ሚና ያለው መሆኑን እንደሚገነዘቡና የታዳሽ ኢነርጂ ለአፍሪካ ሃገራት እድገት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል።

ተቋሙ  በአፍሪካ ኀብረት የአባል ሃገራት በኢነርጂ መሠረታዊ ልማት ግንባታና ትስስር እንዲጎለብት መረጃዎችን በመሰብሰብና በመተንተን ለአባል ሃገራቱ የውሳኔ ሰጪ አካላት የሚያቀርብና በአባል ሃገራቱ መካከልም ሁለንተናዊ ትብብር ለማድረግ የተቋቋመ ተቀማጭነቱም አልጄሪያ አልጀርስ ከተማ ያደረገ የአፍሪካ ህብረት ተቋም መሆኑን አልጀሪያ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.