Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብ ውሃ በሚተኛበት አካባቢ ሁለተኛው ዙር የደን ምንጣሮ ለማካሄድ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለፀ

የአዲስ አበባ፣ ህዳር 19፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዳሴ ግድብ ውሃ በሚተኛበት አካባቢ ሁለተኛው ዙር የደን ምንጣሮ ለማካሄድ የካርታ ስራ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሥራ እድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።

በመጀመሪያው ዙር አንድ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ደንና ቁጥቋጦ ምንጣሮ መካሄዱ ተመልክቷል።

የኤጀንሲው ዳይሬክተር አቶ በሽር አብዱራሂም እንደተናገሩት፥ ሁለተኛው ዙር የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት በተያዘው ዓመት መጨረሻ እንደሚከናወን ይጠበቃል።

“ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ሲከናወን ውሃ የሚተኛበት አካባቢ የሚገኘውን ደን እና ቁጥቋጦ ለመመንጠር የሚያስችል በ”ጂ.ፒ.ኤስ.” ተክኖሎጂ የታገዘ ካርታ እየተዘጋጀ ይገኛል” ብለዋል።

የካርታ ዝግጅት ሥራው ከአንድ ሳምንት በኋላ እንደሚጠናቀቅም አቶ በሽር ጠቁመዋል።

የካርታ ስራው በተያዘለት ጊዜ ሲጠናቀቅ የሚመነጠረው ደን እና ቁጥቋጦ ቦታ ስፋት፣ ስራው የሚጠናቀቅበት ጊዜ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ዝርዝር ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።

በሁለተኛው ዙር ምንጣሮ ከ3 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.