Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ውይይት ያለስምምነት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 30 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአዲስ አበባ ሲያካሂዱት የቆዩት የሶስትዮሽ ውይይት ያለስምምነት ተጠናቋል።

የሶስትዮሽ ውይይቱ መጠናቀቁን ተከትሎ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ውይይቱ ያለስምምነት የተጠናቀቀው ግብፅ የግድቡን የውሃ ሙሌት በተመለከተ አዲስ ሃሳብ ይዛ በመቅረቧ መሆኑን ተናግረዋል።

ትናንት በተጀመረው አራተኛው ዙር የሶስቱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ግብፅ ግድቡ ከ12 እስከ 21 ዓመት እንዲሞላ የሚል አዲስ ሀሳብ ማቅረቧ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ በበኩሏ ይህን ሃሳብ በማንኛውም መልኩ እንደማትቀበል መግለጿን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።

ሶስቱ ሀገራት ከዚህ በፊት የህዳሴው ግድብ በ7 ዓመት ውስጥ እንዲሞላ ስምምነት ላይ ደረሰው የነበረ መሆኑ ይታወሳል።

በቀጣይም የሶስቱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች የእስካሁኑን የሶስትዮሽ ስብሰባ ሂደት ሪፖርት ለሀገራቱ መሪዎች የሚያቀርቡ ይሆናል።

በተጨማሪም ሚኒስትሮቹ የፊታችን ሰኞ ወደ ዋሽንግተን በማምራት የአለም ባንክ ፕሬዚዳንት እና የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሃላፊ በተገኙበት በተካሄዱት አራት የቴክኒክ ስብሰባዎች ዙሪያ ገለፃ ያደርጋሉ።

በዚህ ውይይት ላይም የሶሰቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚገኙ መሆኑ ተመላክቷል።

በፋሲካው ታደሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.