Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የነበሩበትን ችግሮች ስር ነቀል ለውጥ በማድረግ ስራው በተሻለ ሁኔታ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የነበሩበትን ችግሮች ስር ነቀል ለውጥ በማድረግ ስራው በተሻለ ሁኔታ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

በኢፌዲሪ ህዝብ ተወካዮች ምር ቤት የተፈጥሮ ሀብት፣ የውሃ መስኖና ኢነርጅ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፕሮጀክቱ የደረሰበትን ደረጃ በስፍራው በመገኘት የመስክ ምልከታ አድርጓል።

በጉብኝቱም በፕሮጀክቱ ውስጥ ባለፉት ዓመታት የነበሩትን መሰረታዊ ችግሮች በመቅረፍ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜና የጥራት ደረጃ እንዲጠናቀቅ በአመራሩ በተደረገው ከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር በአሁኑ ወቅት ተስፋ ሰጭ አፈጻጸም እየታየ መሆኑን ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴው ቡድን መሪ አቶ ሽመልስ አበባው፥ በፕሮጀክቱ ዙሪያ የሚናፈሰው መሠረተ ቢስ ወሬ ተስፋ የሚያስቆርጥ እንደነበረ አስታውሰል።

ቋሚ ኮሚቴው በአካል ተገኝቶ ባደረገው ምልከታ የኘሮጀክቱ ሥራ ያለበት ደረጃ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ያብራሩት አቶ ሽመልስ፤ የአመራሩ ርብርብ፣ ጥረትና ቅንጅት ተጠናክሮ ሊቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።

መሰራት ሲገባቸው ወደኋላ የቀሩትን ስራዎች አመራሩ ከማኔጅመንቱ እና ከሰራተኛው ጋር በቅንጅት እና ልዩ ትኩረት በመስጠት በየቀኑ የስራውን ሂደትና ውጤት እየተገመገመ በርብርብ እየተሰራ መሆኑን ማረጋገጣቸውንም አንስተዋል።

የኤሌክትሮ መካኒካል ስራውና የብረታብረት ስራው አፈጻጸም ከሲቪል ስራው ጋር ሲነጻጸር ዝቅጠኛ በመሆኑ በልዩ ትኩረት መሰራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ሰራተኞች የሚያነሷቸውን አንዳንድ ጥያቄዎችንም ራሱን ሰራተኛውን የመፍትሄ አካል አድርጎ በማሳተፍ በውይይት መፍፈታት ይገባል ነው ያሉት አቶ ሺመልስ።

በተጨማሪም በአካባቢው ከተነሽ አርሶ አደሮች ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመብራት፣ የንጹህ ውሃ አቅርቦት እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እንዲሁም የካሳ ጥያቄዎችን ከክልሉ አማራሮች ጋር በመናበብ ፈጣንና ተገቢ የሆነ ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አንጂነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው፥ የግድቡ የሲቭል ስራው 85 ነጥብ 5 በመቶ፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራው 29 በመቶ እንዲሁም የብረታብረት ስራው 15 በመቶ መጠናቀቁን አስረድተዋል።

አጠቃላይ የግድቡ አማካይ አፈጻጸም 7ዐ በመቶ መድረሱን የገለጹት ኢንጂነር ክፍሌ፥ እስካሁን 99 ቢሊየን ብር ወጪ መደረጉንና ግድቡን ለማጠናቀቅ 40 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስራ 2015 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው ማስረዳታቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

2013 ዓ.ም ማብቂያ ዩኒት 9 እና 10 ሃይል ለማመንጨት የሚያስችል ውሃ የመያዝ ስራ እንደሚከናወን የገለጹት ስራ አስኪጁ፥ሁለቱ ዩኚቶች 750 ሜጋ ዋት የሚደርስ ሃይል ማመንጨት የሚጀምሩ መሆኑን ነው ያብራሩት።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.