Fana: At a Speed of Life!

የለውጥ ምሰሶዎችን የማጠናከር ስራዎች በተለያዩ ዘርፎች እየተከናወኑ ናቸው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናትና ምሽት ከኢቢሲ ጋር አዲስ ዓመትን አስመልክቶ ቆይታ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው ለውጡን በተመለከተ እንዲሁም በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለቀረቡላቸው ጥይቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

በትግራይ ክልል ከሚካሄደው ምርጫ እና ከህወሃት ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምለሽ።

”ከትግራይ ክልል ጋር ያለው ግንኙነት የምናየው እና የምናስበው በትግራይ ካለው ህዝባችን አንፃር ነው‘ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

”ማንኛውም የምንወስደው እርምጃ የትግራይን ህዝብ ይጠቅማል፤ ይጎዳል፤ በዚህ ሂደት የትግራይ ህዝብ ጥቅሙ በፍጥነት ይረጋገጣል ወይስ ጉዳቱ ያመዝናል እያልን ነው የምናየው‘ ብለዋል።

”ህዝቡ ዲሞክራሲንና ብልፅግናን ይፈልጋል የትግራይ ህዝብ እና በትግራይ ህዝብ ላይ የተደራጀውን ቡድን የሚለይ እሳቤ ከሌለ ቡድኑ ላይ እርምጃ ለመውሰድ በምታደርገው ጥረት ላይ ህዝቡን መጉዳት ተገቢ አይደለም‘ ነው ያሉት።

”የትግራይ ህዝብ ህዝባችን ነው፤ ህዝባችንን የሚጎዳ እርምጃ ወስድን ጥፋት ማካሄድ እና ነገም የሚያስቆጭ ነገር ማስቀጠል አንፈልግም‘ ሲሉ ገልፀዋል።

በትግራይ ክልል የሚካሄደውን ምርጫ በተመለከተ በሰጡት ምላሽም ”የትግራይ ክልል ምርጫ የጨረቃ ምርጫ ነው፤ የጨረቃ ቤት ያላቸው አካላት ህገ ወጥ መሆናቸውን ስለሚያውቁ ኮሽ ባለ ቁጥር ይደነግጣሉ፤ ሲኖትራክ ሲያልፍ ዶዘር መጣ ሊያፈርሰን ነው ብለው ይፈራሉ ነው‘ ያሉት።

ምክንያቱም በኢትዮጵያ ምርጫ ማካሄድ የሚቻለው በምርጫ ቦርድ በኩል እንደሆነ በመግለፅ።

ለኢትዮጵያ ህዝብና ለፓለቲካ ፓርቲዎች ባስተላለፉት መልዕክት አሁን የሚደረጉ የእቁብ ወይም የእድር ስብስቦች እና ጉባኤዎች የእኛ የራስ ምታት ሊሆኑ አይገባም ብለዋል።

አሁንም ህወሃት ነው እየመራ ያለው የጨረቃ ምርጫው ከተካሄደ በኋላም ህወሃት ነው ሚመራው፤ በቀጣይ በፓርላማም ይሁን በአጠቃላይ ሁሉም ምርጫዎች የማይሳተፍ ከሆነ ተቀባይነት አይኖረውም ነው ያሉት።

በቀጣይ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ የማይወዳደር ፓርቲ ውክልና ኖሮት ፓርላማ ሊገባ እንደማይችልም በማንሳት።

በትግራይ ክልል የውሃ፣ የጤና ችግር እና ህዝቡ የሚፈልጋቸውን ልማቶች እንዳላገኘ በመግለፅ እኛ ያን ችግር መፍታት ላይ ማተኮር እያለብን ጉልበት እና አቅም ስላለን ወደ ውጊያ ብንሄድ ማህበረሰቡን ለበለጠ ድህነት የሚዳርግ ስለሆነ በጥበብ እና ብልሃት ማየት እንደሚገባ ተናገረዋል።

”ለኢትዮጵያ ውጊያ አያስፈልጋትም እኔ ለትግራይ የፊት ማስክ እንጂ ጥይት አልክም‘ በማለት ተናገረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ”በጨለማ ካለ ሀይል ጋር መቆየት መንደፋደፍ አያስፈልግም፤ ጭንቅላቱ ደርቋል ኪሱ እየደረቀ ሲሄድ እያየነው ይጠፋል፡፡ ለዚህ ብለን ጊዜ አናጠፋም የቁራ ጩኸት ስለሆነ፡፡የጀመርነውን የብልፅግና መንገድ መቀጠል ነው የምንፈልገው‘ ብለዋል።

ከአዲስ አመት ጋር በተያያዘም ”አዲስ ዓመት የማየው እንዳለፈ እና እንደሚመጣ ጊዜ ነው፤ ሁሉም ጊዜ ተለክቶ ሁሉም ጊዜ በውስጡ ሊይዛቸው የሚገባቸውን ነገሮችን ቀምሮ እንደተሰጠን አምናለሁ‘ ነው ያሉት።

ትናንት በራሱ ሙሉ ነበር፣ ዛሬም በራሱ ሙሉ ነው ፣ ነገም በራሱ ሙሉ መሆኑ ይሰማኛል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዚህ ውስጥም ማለፍ እና መምጣት አለ ፤ በማለፍ ውስጥ ለዛሬ የሚያግዙ ልምዶች ፣ ሀብቶች እና እውቀቶች እንደሚገኙ አንስተዋል።

በማለፍ ውስጥ ዛሬን ለመስራት መነሻ የሚሆኑ ወረት ያከማቸን ፣ ያሰባሰብን እሱን ለመጠቀም የሚያስችል ልምድ እንዳለ አምናለሁም ብለዋል።

በማለፍ ውስጥ የባከኑ ጊዜያት፤ ውዝፍ እዳ የሆኑ ፣ ትናንት ሊሰሩ ሲገቡ ሳይሰሩ አድረው ለዛሬ እና ለነገ ውዝፍ እዳዎች እንደሚኖሩ ገልፀዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ እና አስፈላጊነቱን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ ለውጥ አስፈላጊ ያደረገው ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የሚያቆሟት ምሰሶዎች ጠንካራ ስላልነበሩ መሆኑን ገልፀዋል።

ከለውጡ በኋላ የለውጥ ምሰሶዎቹን የማጠናከር ስራ በተለያዩ ዘርፎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ያነሱ ሲሆን ይህም የተቋም ግንባታን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ውጤትን እያስመዘገበ እንደሆነ አንስተዋል።

ለውጥ እንከን አልባ ሊሆን አይችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት እየተካሄደ ያለው ለውጥ በርካታ በጎ ነገሮች እንዳሉት ጠቁመዋል።

የህዳሴ ግድብን በተመለከተም የግንባታ ሂደት ከለውጡ በፊት ችግር እንደነበረበት የሚታወቅ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በመንግስት ስልጣን ላይ የነበሩ የተወሰኑ ቡድኖች የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርም ሆኑ የውሃ ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ችግሮችን እንዳይፈቱ ምክንያት ሆነው ነበር ብለዋል።

የአመራር ችግር እንደነበረ በመግለፅ ይህን ችግር ለመቅረፍ ስራ በመሰራቱ በግንባታ ሂደቱ ላይ ውጤት መታየቱን አንስተዋል።

በነበረው አመራር ቢቀጥል ኖሮ የህዳሴ ግድብ ፤ እንኳን ዘንድሮ በሶስት ዓመት ውስጥም ውሃ ሊይዝ አይችልም ነበር ብለዋል።

ከፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ በሰጡት ምላሽ በኢትዮጵያ ከመንገድ ጋር በተያያዘ በርካታ ጥያቄዎች እና አጨቃጫቂ ነገሮች እንደሚነሱ በመግለፅ አሁን ላይ ለጥያቀዎቹ ምላሽ እየተሰጠ እንደሆነ ገልፀዋል።

ሀይልን በተመለከተ ሶስት ዓመት ሙሉ ቆሞ የነበረውን ኮይሻ መጀመሩን ፤ ነገሌ ዳዋ ፕሮጀክቱ አልቆ ውሃ መያዝ ስላልቻለ ስራ ላይ እንዳልነበረና አሁን ውሃ ይዞ ሀይል እያመነጨ መሆኑን እና የህዳሴ ግድብ የደረሰበት ደረጃም እንደሚታወቅ አብራርተዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢትዮጵያ ውስጥ 12 ብቻ ነው የነበሩት አሁን ሁሉም ተጠናቀዋል ያሉ ሲሆን፥ የስኳር ፋብሪካዎች በአብዛኛው በከፍተኛ ፍጥነት እንደተሰሩና በዘንድሮው ዓመትም 600 ሺህ ኩንታል ስኳር ተጨማሪ ምርት እንደተመረተ አብራርተዋል።

ከበጀት ውጭ ሀብትና ዕውቀት አስተባብረን ደግሞ ሀገር የሚቀይር ገፅታ መፍጠር እንችላለን በሚል ሀሳብ የሸገር ፕሮጀክትና እንጦጦ ፓርክን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

”ሸገርና እንጦጦ አንድ ብር ከመንግስት ወጪ አልተደረገም፤ ሙሉ በሙሉ ሰዎችና የሚረዱን አካላት አግዘውን ነው እየተሰራ የሚገኘው‘ ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በኤፍሬም ምትኩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.