Fana: At a Speed of Life!

የላሊበላ ቤተክርስቲያን ጥገና እና የዘላቂ ቱሪዝም ልማት ሥራ ተጠናክሮ በሚቀጥልበት አግባብ ላይ በፓሪስ ውይይት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የላሊበላ ቤተክርስቲያን ጥገና እና የዘላቂ ቱሪዝም ልማት ሥራ ተጠናክሮ በሚቀጥልበት አግባብ ላይ በፓሪስ ከተማ ምክክር እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ውይይቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በትብብር ለመሥራት የደረሱበትን ሥምምነት ተከትሎ የተጀመረ ነው፡፡

ኢማኑኤል ማክሮን የቅዱስ ላሊበላን ቤተክርስቲያን እንዲጎበኙ እና ለቅርስ ጥበቃ ሥራ ድጋፍ እንዲያደርጉ ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል፡፡

ሥራውን በተደራጀና በተቀላጠፈ መንገድ ለመተግበር እንዲቻል ከቱሪዝም ሚኒስቴር በተጨማሪ በአዲስ አበባ የሚገኘዉ የፈረንሳይ ኤምባሲ እንዲሁም በፓሪስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከፍተኛ ድጋፍ እያደርጉ እንደሚገኝ ከባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የጥገና ሥራው እንደ ሀገር የተያዘውን የቱሪዝም ልማት ርዕይ ለማሳካት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋልም ተብሏል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስቴር ዴኤታ፣ የቅርስ ጥበቃ ዋና ዳይሬክተር ፣ የቅዱስ ላሊበላ ደብር ዋና አስተዳዳሪ እና የፈረንሳይ የላሊበላ ዘላቂ ፕሮጀክትአስተባባሪ በፓሪስና ቦርዶ ከተሞች ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ጉብኝት እያካሄዱ ነው፡፡

ልዑካኑ በፈረንሳይ የተገኙት በሀገሪቷ እየተከናወኑ ያሉ የቅርስ ጥበቃና የቱሪዝም ልማት ሥራዎችን ለማየትና ተሞክሮ ለመውሰድ ብሎም ከፈረንሳይ ዩኒቨርሲቲዎችና የጥገና እና የቴክኒክ ቡድኖች ጋር በመወያየት በላሊበላ እና በሌሎች የኢትዮጵያ ቅርሶች ላይ ጥገና ማድረግ በሚቻልበት አግባብ ላይ ለመመካከር መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.