Fana: At a Speed of Life!

የልማት፣ የዴሞክራሲና የሰላም ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አቅጣጫ አስቀመጠ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 27፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የልማት፣ የዴሞክራሲና የሰላም ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አቅጣጫ አስቀመጠ።

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት በተለያዩ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሲያካሂድ የነበረውን መደበኛ ስብሰባ ማጠናቀቁን አስታውቋል።

የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፥ ፓርቲው ህዳር 25 እና 26 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባው በሶስት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ውይይት አካሂዷል ብለዋል።

አጀንዳዎቹም፥ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ፣ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን እንዲሁም የብልፅግና ፓርቲ ለ2013 የምርጫ ዝግጅትና ቅስቀሳን የተመለከቱ ናቸው።

በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ በደረገው ውይይት፥ አጥፊው የህወሓት ጁንታ ቡድን በሰሜን እዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ፤ መንግስት ተገዶ ህግን ወደ ማስከበር ስራ መግባቱን አስታውሰዋል።

አጥፊው የህወሓት ጁንታ በማይካድራ በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈፀመው ጥቃት እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት በሌሎች አካባቢዎች ላይ በእጅ አዙር በንፁሃን ዜጎች ላይ ሲፈፅማቸው የነበሩ ተግባራት ተስፋ በመቁረጥ የፈፀመው እና በቀጥታ ቡድኑ ማንነቱ እንዲታወቅ ያደረገ መሆኑን በስብሰባው እንደተገመገመም እንስተዋል።

እንደ አጠቃላይ የህግ የማስበር ዘመቻው ስኬታማ እንዲሆን የአማራ ልዩ ሀይል እና ሚሊሻ፣ የአፋር ልዩ ሀይል እንዲሁም የቁሳቁስ እና የሞራል ድጋፍ ሲያደርግ ለነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ በተጨማሪም የጁንታውን ፕሮፖጋንዳ ባለመቀበል ከመከላከያ ሰራዊት እና ከመንግስት ጎን ለነበረው የትግራይ ህዝብ ፓርቲው ያለውን ክብር አቅርቧል።

የጥፋት ቡድኑ አስተባባሪዎችን ለህግ የማቅረብ ሂደቱ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ በፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ አቅጣጫ መቀመጡንም አስታውቀዋል።

በህግ ማስከበር ሂደቱ የተጎዱ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱና እንዲቋቋሙ፣ የወደሙ መሰረተ ልማቶች ቶሎ ተስተካክለው ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ አንዲሁም የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በፍጥነት መደበኛ አገልግሎት ወደመስጠት ስራ እንዲመለሱ አቅጣጫ መቀመጡንም ጠቅሰዋል።

በየአካካቢው የሚካሄዱ የልማት፣ የዴሞክራሲ እና የሰላም ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አቅጣጫ ማስቀመጡንም አቶ ብናልፍ ገልፀዋል።

ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በተመለከተም ብሄረ መንግስት እና ሀገረ መንግስት በመገንባት ሂደት ውስጥ ፅንፍ የወጡ አስተሳሰቦች እንደሚስተዋሉ የተመለከተው ስራ አስፈፃሚው፤ ይህንን ለማስተካከል ህዝቡ ፖለቲካዊ ንቃት እንዲኖረው መሰራት እንዳለበት ገምግሟልም ነው ያሉት።

ከዓለም ዓቀፋዊ ሁኔታዎች አንፃር በተለይም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ፥ ከአባይ ፖለቲካ ጋር በተያያዘ የህዳሴ ግድብ እንዳይጠናቀቅ እና የሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዳይደርስ የሚከፈቱ ፕሮፖጋንዳዎች ላይ በዝርዝር ውይይት ተደርጎ ግልፅ አቅጣጫ መቀመጡንም አስረድተዋል።

ምርጫን በተመለከተም የ2013 ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድም ሆነ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ እንዲሆን አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የሚጠበቅበትን ሁሉ አሟልቶ በዚህ ሂደት ውስጥ ለማለፍ ዝግጅት ማድረጉንም የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ምርጫውን ለማሸነፍ ማኒፌስቶ አዘጋጅቶ ወደ ምርጫ ቅስቀሳ እንደሚገባም አብራርተዋል።

በትዝታ ደሳለኝ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.